የመስቀል ደመራ በዓል ታሪክና አከባበር

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

የመስቀል ደመራ በዓል ታሪክና አከባበር

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ከወደቀበት መርገም ያድነው ዘንድ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ በ33 ዓመቱ በራሱ ፈቃድ በመስቀል ላይ ተሰቀለ፡፡ በመገረፉ ቁስል እኛ ተፈወስን (1ጴጥ 2፥24):: በስቅለቱም ዲያብሎስን ድል ነሥቶ በወህኒ /በሲዖል/ ለነበሩ ነፍሳት ነጻነትን ሰበከላቸው (1ጴጥ 3፥18-19):: የሰው ልጅ በሙሉ ከዲያብሎስ ባርነት ፍጹም ነጻ ወጣ:: ሰላምንም ያደርግ ዘንድ ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ ሕዝብና አሕዛብን በአንድ አካል ከራሱ ከእግዚአብሔር ጋር አስታረቀ (ኤፌ 2፥16)፡፡ ከፍተኛ ወንጀል የሠሩ ሰዎች ብቻ ይሰቀሉበት የነበረው መስቀል ከጌታ ስቅለት በኋላ የመዳን ምልክት ሆነ::

ዳሩ ግን ጌታ የተሰቀለበት መስቀል ተአምራትን በማድረጉ የታወኩ አይሁድ መስቀሉን ከሰዎች እይታ ለመሠወር ወሰኑ:: ጉድጓድ ቆፍረው ቀበሩት:: መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ ለ300 ዓመታት ያህል የቆሻሻ መጣያና ማከማቻም አደረጉት:: ምንም እንኳን አይሁድ ለጊዜው መስቀሉን ከዐይን ለመሰወር ቢችሉም ከክርስቲያኖች ልቡና ግን ሊያወጡት አልቻሉም:: የመስቀሉ ብርሃን በልቡናቸው የሚያበራ ክርስቲያኖች እየበዙ መጡ:: መስቀሉንም መፈለግ ጀመሩ::

የንግሥት እሌኒ ድካምና ፍሬ

ንግሥት እሌኒ ልጇን ቆስጠንጢኖስን ከልጅነቱ ጀምሮ ስለ ክርስትና ሃይማኖትና ስለ ክርስቲያኖች መከራ ታስተምረው ስለነበር በክርስቲያኖች ላይ የነበረው አመለካከት በሮም ከነገሡት ቄሣሮች ሁሉ የተሻለ ነበር፡፡ ቆስጠንጢኖስ የሮም ንጉሠ ነገሥት ከሆነ በኋላ በ300 ዓመታት ውስጥ ለመጀመርያ ጊዜ ለክርስቲያኖች የነጻነት ዐዋጅ ዐወጀ፡፡ ክርስትናም ብሔራዊ ሃይማኖት ሆነች፡፡ ንግሥት እሌኒም የተፈጠረውን አመች ሁኔታ በመጠቀም የጌታችንን መስቀል ከተቀበረበት ለማውጣት በ327 ዓ/ም ወደ ኢየሩሳሌም ሔደች፡፡

ንግሥት እሌኒ ልጇ ቆስጠንጢኖስ ክርስቲያን ከሆነላት ወደ ኢየሩሳሌም ሔዳ መስቀሉን ለመፈለግ እንዲሁም በኢየሩሳሌም ያሉ ቅዱሳት መካናትንና አብያተ ክርስቲያናትን ለማሳነፅ ለእግዚአብሔር ተሳለች፡፡ ከዚህ በኋላ ቆስጠንጢኖስ አምኖ በ337 ዓ/ም ተጠመቀ፡፡ ቅድስት እሌኒም ወደ ኢየሩሳሌም ሔደች እንደደረሰችም ስለ ክብረ መስቀል መረመረች ጠየቀች፡፡ ቦታውን የሚያስረዳት ግን አላገኘችም፡፡ አይሁድ የተቀበረበትን ቦታ ለማሳየት ባይፈልጉም በኋላ ባደረገችው ጥረት አረጋዊው ኪራኮስ የጎልጎታን ኮረብታ አመላከታት ዳሩ ግን ኪራኮስ ዘመኑ ከመርዘሙ ጋር ተያይዞ በአካባቢው ከነበሩት ከሦስቱ ተራሮች ውስጥ መስቀሉ የሚገኝበት የትኛው እንደሆነ ለይቶ ማወቅ አልቻለም፡፡

ንግሥት እሌኒ ከሦስቱ ተራሮች የቱ እንደሆነ ለመለየት በእግዚአብሔር መልአክ እርዳታ ደመራ አስደምራ ብዙ እጣንም በመጨመርና በማቃጠል ጸሎት ተያዘ፡፡ የእጣኑ ጢስ ወደ ሰማይ በመውጣት በቀጥታ ተመልሶ መስቀሉ ባለበት ተራራ ላይ በማረፍና በመስገድ መስቀሉ ያለበትን ትክክለኛ ስፍራ አመለከታት፡፡ ቅዱስ ያሬድም ጢሱ ሰገደ ብሎታል፡፡ ከዚያም መስከረም 16 ቀን ቁፋሮው እንዲጀመር አዘዘች፡፡ ሰባት ወር ያህል ከተቆፈረ በኋላ መጋቢት 10 ቀን ሦስት መስቀሎች በአንድነት ተገኙ፡፡የክብር ባለቤት ጌታችን የተሰቀለበት የትኛው እንደሆነ ለማወቅ ተቸገሩ፡: መስቀሎቹን ወስደው በሞተ  ሰው በተራ ቢያስቀምጡ ጌታችን የተሰቀለበትና በዕለተ ዐርብ ተሰቅሎ የዋለበትና በደሙ መፍሰስ የተቀደሰው መሰቀል የሞተውን ሰው በማስነሣት በሠራው ተአምር ሌሎቹ ሁለቱ ታምራት ባለማድረጋቸው የጌታን መስቀል ለይቶ ማወቅ ተችሏል። እሌኒና ክርስቲያኖች ሁሉ ለመስቀሉ ሰገዱለት፡፡ በየሀገሩ ያሉ ክርስትያኖች ሁሉ የመስቀሉን መገኘት በሰሙ ጊዜ መብራት አብርተው ደስታቸውን በመግለጥ ለዓለም እንዲታወቅ አደረጉ፡፡ ንግሥት እሌኒ ለመስቀሉ ቤተ መቅደስ ከሠራችለት ጊዜ ጀምሮ በመስከረም 17 ቀን አሁን በኢትዮጵያ እንደሚከበረው በክርስቲያኖች ዘንድ መስቀል ይከበር ነበር።

ግማደ መስቀሉ ወደ ኢትዮጵያ እንዴት መጣ? 

የጌታ መስቀል ለብዙ ዓመታት በኢየሩሳሌም ከቆየ በኋላ ነገሥታት መስቀሉን ለመውሰድ ጠብ ፈጠሩ፡፡ በዚህ ጊዜ የአንጾኪያ፣ የኤፌሶን፣ የአርማንያ፣ የግሪክ፣የእስክንድርያ፣ የመሳሰሉት የሃይማኖት መሪዎች ጠቡን አበረዱት:: ከዚያም አያይዘው በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የክርስቶስን መስቀል ለዐራት ከፍለው በስምምነት ተካፍለው ከሌሎች ታሪካዊ ንዋያተ ቅድሳት ጋር በየሀገራቸው ወስደው በክብር አስቀመጡት:: የቀኝ ክንፉ የደረሰው ለአፍሪቃ ስለነበር ከታሪካዊ ንዋየ ቅድሳት ጋር በግብፅ የሚገኘው የእስክንድርያ ፓትርያርክ ተረክቦ ወስዶ በክብር አስቀመጠው፡፡

ኢትዮጵያዊው ንጉሥ ዳግማዊ ዳዊት የግብፅ ክርስቲያኖች በአማሌቃውያን ከሚደርስባቸው ተጽዕኖ ነጻ እንዲወጡ በማድረጋቸው የግብፅ ፓትርያርክ የከበሩ ስጦታዎችን ላኩላቸው:: ንጉሥ ዳግማዊ ዳዊት ግን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የምትፈልገው ወርቅ ሳይሆን ጌታ የተሰቀለበትን መስቀሉን እንደሆነ ገለጹላቸው:: በመሆኑም የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ግማደ መስቀሉን ከሌሎች ንዋየ ቅድሳት ጋር ለኢትዮጵያ ሰጥታለች:: ይህ ግማደ መስቀል በግሸን ማርያም ገዳም በእግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን ሆኖ ኢትዮጵያን እየባረከ ይገኛል::

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መስቀልን ከሐዋርያት በተማረችው መሠረት የወርና የዓመት በዓል ሠርታ ታከብረዋለች:: መስከረም 16 ቀን ደመራ ደምራ ጸሎትና ምሥጋና ታቀርባለች። ቅዱስ መስቀል ከተቀበረበት መሬት በእሌኒ አማካኝነት መገኘቱን ስታስብ በአሁኑ ዘመን ከብዙ ሰዎች ልቡና የተሠወረው መስቀል እንዲገለጥላቸው ትጸልያለች:: በመስቀል የሚገኘውን በረከት እየተቀበለች በመስቀል የሚመሰለውን መከራ ሁሉ ትታገሣለች:: መስቀል በካህናት በምእመናንና በምእመናት ልቡና ተስሏል:: በአንገታቸውና ልብሳቸውም መስቀል አለ:: ሥራ ሲጀመርና ምግብ ሲቀርብ በመስቀል አምሳያ ይማተባል:: መስቀል ለሁሉም ነገር መጀመሪያና መጨረሻ  ነው:: “እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ” (ማቴ 16፡24) እንዳለ ጌታችን ቤተ ክርስቲያናችን ዕለት ዕለት መስቀሉን ትሸከማለች።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ መስከረም 16 ቀን የምትደምረው ደመራ አገራዊ አንደምታም አለው:: የመስቀል ደመራ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት: የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) እውቅና ተሰጥቶት ዓለም አቀፋዊ ቅርስ ተብሎ ተመዝግቧል::

ከሀገር ቤት ርቀን የምንገኝ ኢትዮጵያውያንም የበዓሉን ታላቅነት ለልጆቻችንና ለምንኖርበት የኖርዌይ ኅብረተሰብ ማስረዳትና የበዓሉ ታዳሚ እንዲሆኑ ማድረግም ይጠበቅብናል። «የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚብሔር ኃይል ነው» (1ቆሮ 1፥18) እያልን ልናከብረውና ልንጠብቀው ይገባናል።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

በኖርዌይ ኦስሎ መ/ቅ/ ቅዱስ ገብርኤልና አቡነ ተክለ ሃይማኖት የኢትዮጵያ ኦ/ተ/ ቤተ ክርስቲያን ስብከተ ወንጌል ክፍል የተዘጋጀ

2012 ዓ/ም