ጥምቀት

፩ የወልደ እግዚአብሔር ጥምቀት

ለምን ተጠመቀ?

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሠላሳ ዘመኑ በእደ ዮሐንስ በፈለገ ዮርዳኖስ ተጠምቋል። ለምን ተጠመቀ? የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም የተጠመቀው እንደ አይሁድ ሥርዓት ለመንጻት፣ እንደ ዮሐንስ ጥምቀት ለሥርየተ ኃጢአት አልነበረም። ነገር ግን ስለሚከተሉት ምክንያቶች ተጠምቋል።

 . ፩ ትሕትናን ለማስተማር

መምህረ ትሕትና የሆነው መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለተከታዮቹ አርአያ ይሆን ዘንድ የእጁ ፍጥረት በሆነው በአገልጋዩ በዮሐንስ እጅ ተጠምቋል። መጥምቀ መለኮት ዮሐንስ እኔ በአንተ ልጠመቅ ይገባኛል እንጂ አንተ በእኔ እንዴት ትጠመቃለህ? ብሎ ለማጥመቅ ፍቃደኛ አለመሆኑን ቢናገር ጌታ “አሁንስ ፍቀድልኝ እንዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናል” በማለት እንዲያጠምቀው ያዘዘው መጠመቁን ለተከታዮቹ ትሕትናን ለማስተማር እንደሆነ አስረድቷል። ማቴ ፫ ፥ ፲፭።

.፪ አርአያ ለመሆን

ጥምቀት ዳግመኛ ከእግዚአብሔር የምንወለድበት ማለትም የልጅነት ጸጋን የምንጎናጸፍበት ምሥጢር ነው። ያለጥምቀት የዘላለም ሕይወት አናገኝም ስለዚህ ሰው ሁሉ መጠመቅ ግድ ስለሆነ እርሱ ራሱ በመጠመቅ ለእኛ አርአያ ሆኖናል።

.፫ የዕዳ ደብዳቤያችንን ለመደምሰስ

ጥንተ ጠላት ዲያብሎስ አዳምና ሔዋንን ካሳተ በኋላ በጨለማ መጋረጃ ጋርዶ አገዛዙን አጸናባቸው። ኋላም በሥቃይ ላይ ላሉት አዳም እና ሔዋን የእርሱ ባሪያዎች መሆናቸውን አምነው የባርነት ማረጋገጫ ደብዳቤያቸውን በዕብነ ሩካብ ጽፈው ቢያመጡለት አገዛዙን እንደሚያቀልላቸው ነገራቸው። እነርሱም እውነት መስሎአቸው “አዳም የዲያብሎስ ወንድ አገልጋዩ ፣ ሔዋን የዲያብሎስ ሴት አገልጋዩ” ብለው በሁለት ዕብነ ሩካም ጽፈው ሰጥተውታል። ዲያብሎስም አንዱን በዮርዳኖስ አንዱን በሲኦል አስቀምጦት ነበር። ጌታም በተጠመቀ ጊዜ ዮርዳኖስ ያለውን የዕዳ ደብዳቤ እንደሰውነቱ ተረግጦ እንደ አምላክነቱ አቅልጦ አጥፍቶታል። በሲኦል የተጣለውን በዕለተ ዓርብ በአካለ ነፍስ ወርዶ ነፍሳትን ሲያወጣ አጥፍቶታል። ቆላ. ፪ ፥ ፲፫ – ፲፭

. ፬ አንድነቱንና ሦስትነቱን ለመግለጥ

እግዚአብሔር አንድ ሲሆን ሦስት፣ ሦስት ሲሆን አንድ መሆኑ በዘመነ ብሉይ በሁሉም ዘንድ እንደ አዲስ ጎልቶ የማይታወቅ ምሥጢር ነበር። በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ ከሦስቱ አካል አንዱ አካል እግዚአብሔር ወልድ በሥጋ በተገለጠ ጊዜ አንድነቱና ሦስትነቱን ገልጦ አስተምሯል። ሦስትነቱን በትምህርት ከመግለጡ በፊት በጥምቀቱ ወቅት በገሃድ እንዲገለጥ አድርጓል። ሦስቱ አካላት በአንድ ቅጽበት በአንድ ቦታ ማንነታቸውን ገልጠዋል ሜቴ ፫ ፥ ፲፮ ይኸውም አብ በደመና ሆኖ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው ብሎ ሲመሰክር፣ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሣል ወርዶ በራሱ ላይ አርፎ፣ አካላዊ ቃል ክርስቶስ በፈለገ ዮርዳኖስ ቆሞ በመታየት ኅቡዕ የነበረው የሥላሴ ምሥጢር ገሀድ ሆነ።

 

፪ በዮርዳኖስ ወንዝ የተጠቀበት ምክንያት

ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ መጠመቁ የአጋጣሚ ጉዳይ አይደለም። ወይም በኢየሩሳሌም ውስጥ ሌሎች አፍላጋት ባለመኖራቸው እንደዚሁም ዮርዳኖስ የጠለቀ ወንዝ በመሆኑ አልነበረም። የዮርዳኖስ ወንዝን መርጦ የተጠመቀበት መሠረታዊ ምክንያት አለው። ምክንያቶቹም ፦

.፩ ትንቢቱን ለመፈፀም

ትንቢት ድርጊትን ቀድሞ የሚነግር ነው። አማናዊ ትንቢት ጊዜውንና ወቅቱን ጠብቆ መፈጸሙ አይቀሬ ነው። ጌታ በዮርዳኖስ ወንዝ እንዲጠመቅ ድርጊቱ ከመፈጸሙ ከሺህ ዘመን ቀደም ብሎ በቅዱስ ዳዊት አማካኝነት ትንቢት ተነገሮ ነበር። «ባሕር አየች ሸሸችም፤ ዮርዳኖስም ወደ ኋላ ተመለሰ ተራሮች እንደኮርማዎች

ኮረብቶችም እንደጠቦቶች ዘለሉ። አንቺ ባሕር የሸሸሽ፣ አንቺም ዮርዳኖስ ወደ ኋላሽ የተመለስሽ ምን ሆናችኋል። እናንተም ተራሮች እንደ ኮርማዎች ኮረብቶችስ እንደ ጠቦቶች ለምን ዘለላችሁ? ከያዕቆብ አምላክ ፊት» መዝ ፻፲፫ ፥ ፫ -፮

የያዕቆብ አምላክ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ ሲጠመቅ ከላይ የተገለጠው ትንቢት ተፈጻሚነትን አግኝቷል።

.፪ ምሳሌውን አማናዊ ለማድረግ

ፈለገ ዮርዳኖስ ታሪካዊና የእምነት ምልክት ነው። ከእምነት ጋር የተያያዙ አያሌ ድርጊቶች ተፈጽመውበታል።

✔ ኢዮብ ከበሽታው የተፈወሰው በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠምቆ ነው።

✔ኢዮብ የአዳም፣ ደዌ የመርገመ ሥጋ የመርገ ነፍስ፣ ዮርዳኖስ የጥምቀት ምሳሌዎች ናቸው።

✔ እስራኤል ወደ ምድረ ርስት የገቡት ዮርዳኖስን ተሻግረው ነው። ምእመናንም ወደ ርስት ሀገራቸው መንግስተ ሰማያት የሚገቡት በጥምቀት ነው።

✔ አብርሃም ከመልከ ጼዴቅ ጋር የተገናኘው የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግሮ ነው። መልከ ጼዴቅም ዮርዳኖስን ተሻግሮ ለመጣው ለአብርሃም ኅብስተ አኰቴት ጽዋዓ በረከት አዘጋጅቶ ጠብቆታል።መልከ ጼዴቅ የካህናት፣ አብርሃም የምእመናን፣ዮርዳኖስ የጥምቀት፣ ኅብስተ አኮተቴት ጽዋዓ በረከት የሥጋ ወደሙ ምሳሌ ናቸው። ፈለገ ዮርዳኖስ መነሻው አንድ ወንዝ ሲሆን ዝቅ ብሎ በዮርዳኖስ እና በዳሮስ ይለያል። ዮር በእስራኤል በኩል ያለው ሲሆን ዳኖስ በአሕዛብ በኩል ያለው ነው። ወረድ ብሎ ደግሞ ሁለቱም አንድ ይገናኛሉ ። በሚገናኙበት ቦታ ላይ ነው ጌታ የተጠመቀው ይህ ምሳሌነቱ

☞ ዮርዳኖስ ምንጩ ከላይ አንድ እንደሆነ ሁሉ የሰው ዘር ሁሉ ግንድ አንድ አዳም መሆኑን ሲያሳይ፣ ዝቅ ብሎ መከፈሉም እስራኤል በኦሪት አሕዛብ በጣኦት ወይም እስራኤል በግዝረት አሕዛብ በቁልፈት መለያየታቸውን ያሳያል። ዝቅ ብሎ መገናኘቱ ደግሞ በጌታችንና መድኋኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት አምነው በመጠመቃቸው ወደ አንድነት መምጣታቸውን። ጌታ የተጠመቀውም በመገናኛው ነውና ሁሉንም አንድ ሊያደርግ መምጣቱ ያስገነዝባል።

.፫ የዕዳ ደብዳቤያችንን ይደመስስ ዘንድ

 

፫ ጥምቀት ለምን በውኃ ሆነ?

ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀው በውኃ ነው እኛም እንድንጠመቅ የታዘዝነው በውኃ ነው ለምን በውኃ ሆነ ጌታችን ጌትነቱን ለመግለጽ ለምን በወተት ፣ በማር አልተጠመቀም? እኛስ ለምን በውኃ እንጠመቃለን፣ በማር በወተት ለምን አለደረገውም ቢሉ

✔ በኖኅ ዘመን ፍጥረት ሁሉ በውኃ ጠፍቶ ነበር ከዚህም የተነሣ ውኃ ለመዓት እንደተፈጠረ ይታሰብ ነበር። ዳሩ ግን ውኃ ለምሕረትና ለድኅነት የተፈጠረ መሆኑን ለማሳየት ጌታም ጥምቀቱን በውኃ አድርጓል።

✔ ማርና ወተት በማንኛውም ሰው ቤት አይገኙም ውኃ ግን በሁሉም ቤት ይገኛል። ጥምቀት በማር ወይንም በወተት አንዲሆን ቢደረግ ኖሮ ድኅነት ለሀብታሞች ብቻ በሆነ ነበር። በሁሉም ቤት በሚገኘው ውኃ በማድረጉ ጥምቀት ለሀብታም ለድሀ ሳይባል ለሁሉም እኩሉ እንዲደርስ መደረጉን እንረዳለን።

✔ ሌሎች ፈሳሾች አትክልት ላይ ቢያፈሱአቸው አትክልቱን ያደርቃሉ እንጂ አያለመልሙም። ውኃ ግን ያለመልማል እናንተም በውኃ ብትጠመቁ ልምላሜ ሥጋ ልምላሜ ነፍስ ታገኛላችሁ ሲል ነው።

✔ ማርና ወተት ልብስ ቢያጥቡባቸው እድፍ አያጠሩም ውኃ ግን ያጠራል። ከኃጢያት እድፍ በውኃ ተጠምቃችሁ ትጠራላችሁ ለማለት።

✔ ውኃ መልክን ያሳያል እናንተም በውኃ ብትጠመቁ የሥላሴን መልክ በመንፈስ ታያላችሁ ሲል ነው።

✔ ውኃ እሳትን ያጠፋል እናንተም በውኃ ተጠምቃችሁ የልጅነት ጸጋ ካገኛችሁ ከገሃነም እሳት ትድናላችሁ ሲል ነው።

✔ ውኃ ከጽንፍ እስከ ጽንፍ ይደርሳል ጥምቀትም ከጽንፍ እስከ ጽንፍ ተዳርሷል ።

 

ባጠቃላይ የጌታችን መድኃኒታችን ጥምቀት በዓል ከዘጠኙ ዓበይት የጌታችን በዓላት አንዱ ነው። በጥምቀት ልጅነት አግኝተናል። በልጅነታችንም አባታችን ብለን አምላካችንን እንጠራለን። አንዳንዶች በየዓመቱ የምናከብረው ጥምቀት እና በካህናት የተባረከ ውሃ መረጨታችንን እያዩ በየዓመቱ የምንጠመቅ የሚመስላቸው አሉ። ሆኖም የልጅነት ጥምቀት አንዴ የምትፈፀም ነች። ጥምቀት ከማይደገሙ ምስጢራት ውስጥ ነው። ስለሆነም ወንድ በአርባ፣ ሴት በሰማንያ ቀኖች ወደ ቤተ ክርስቲያን መጥተው ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ አንዴ ልጅነት ያገኛሉ ወይንም እኛ ሁላችን አግኝተናል። በየዓመቱ የምናከብረው የጥምቀት በዓል ጌታችን የሰራልንን አምላካዊ ሥራ የምናደንቅበት እና የምናከብርበት፣ በማክበራችንም የምንባረክባት ቀን ነው።

 

ልዑል እግዚአብሔር ከበዓሉ በረከት ይክፈለን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል።