ጾመ ፍልሰታ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

ፍልሰታ ማለት ምን ማለት ነው?

ፍልሰታ የሚለው ቃል የተገኘው ፈለሰ ከሚለው የግዕዝ ቃል የተገኘ ሲሆን በጥሬ ትርጉሙ መለየት፣ማረግ፣ወደላይ መውጣት የሚለውን ትርጉም ይይዛል። በእዚህ መሠረትም ጾመ ፍልሰታ የእመቤታችን ድንግል ማርያምን የሥጋዋ ከመቃብር መለየት እና ማረግን ያመለክታል። ይህ በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከተወሰኑት ሰባቱ አጸዋማት ውስጥ ለዓመቱ የመጨረሻው ጾም ነው።

ፍልሰታ ጾም ለምን እንፆማለን?

የፍልሰታ ጾም ከነሐሴ 1 እስከ 15 የሚጾም ሲሆን በቤተ ክርስቲያናችን አስተምሮ መሠረት እመቤታችን ያረፈችው በጥር 21 ቀን ነው። ሐዋርያትም አስከሬኗን ሊቀብሩ ወደ ጌቴሴማኒ ይዘዋት ሲሔዱ አይሁድ በምቀኝነት ልጇ ከሙታን ተለይቶ ተነሥቷል። አሁንም እርሷ ገቢረ ተአምር ልታደርግ አይደል? ብለው አስከሬኗን ተሸክመው የሚሔዱትን ሐዋርያትን በታተኗቸው። በዚህን ጊዜ መላእክት የእመቤታችንን አስከሬን ከአይሁድ ነጥቀው በገነት አኖሩት። በስምንተኛው ወር በነሐሴ ሐዋርያት ከነሐሴ 1 እስከ 14 ሁለት ሱባዔ ገብተው ከጌታችን ተቀብለው በጸሎትና በምህላ ቀበሯት። በዚህ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ ቶማስ የተባለው ለሐዋርያዊ አገልግሎት ወጥቶ ነበር እና መገኘት አልቻለም ነበር።

እመቤታችን በተቀበረች በሦስተኛው ቀን ከላይ እንደተጠቀሰው በነቢያት ትንቢት እንደተነገረላት እንደ ልጇ ተነሥታ ስታርግ ቶማስ ከሀገረ ስብከቱ በደመና ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ አገኛት። በዚህን ጊዜ ትንሣኤዋን ሌሎች ሐዋርያት አይተው ለእርሱ የቀረበት መስሎት በረከት ቀረብኝ ሲል ተበሳጨ።ቀድሞ የልጅሽን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁ አሁን ደግሞ ያንችን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁ ብሎ እራሱን ከደመና ላይ ሊወረውር ቃጣው። በዚህን ጊዜ እመቤታችን ቶማስን አፅናናችው ከእርሱ በቀር ትንሣኤዋን ያየ አለመኖሩን ነገረችው።ለምስክርነት እንዲሆንም በቀብሯ ጊዜ የነበረውን ሰበኗን ሰጥታው አረገች።

ሞት በጥር፣በነሐሴ መቃብር

ቶማስም ሰበኗን ደብቆ ይዞ ሐዋርያት ካሉበት ደረሰ። ሐዋርያትንም የእመቤታችን ነገር ምን ደረሰ? አላቸው። ሐዋርያትም እመቤታችን ሱባዔ ገብተን ጌታችን አስከሬኗን ከዕፀ ሕይወት አምጥቶ ሰጥቶን በክብር ቀበርናት አሉት። ቶማስም መልሶ ሞት በጥር፣በነሐሴመቃብር?አላቸው።ሐዋርያትም መለሱለት ቶማስ አትጠራጠር። ቀድሞ ጌታችን በተገለጠ ጊዜ ትንሣኤውን ጣቶቼን በተቸነከሩ እጆችህ ካላስገባሁ ብለህ የደረሰብህን ታውቃለህ አሁንም የእመቤታችንን መቀበር አላመንክምን? አሉት። ቶማስ ግን ሐዋርያትን ይዞ ወደ መቃብሯ ሔደ። መቃብሯን ከፍተው ሲመለከቱ ሐዋርያት ደነገጡ። በዚህን ጊዜ ቶማስ አታምኑኝም ብየ ነው እንጂ እመቤታችን አርጋለች። ስታርግም በደመና ከሀገረ ስብከቴ ስመጣ ተገናኘን ለምልክቱም ይኸው የቀበራችሁበት ሰበን አላቸው።ሐዋርያትም ለበረከት ሰበኗን ተከፋፍለው ወደየሀገረ ስብከታቸው ሔዱ።

በዓመቱ ግን ሐዋርያት ተሰበሰቡ እና ትንሣኤሽን ቶማስ አይቶ እኛም በረከት አይቅርብን ብለው ከነሐሴ አንድ ጀምረው ሱባዔ ገቡ።በነሐሴ 14 አስከሬኗን ትኩስ በድን አድርጎ አምጥቶ ሰጥቷቸው ከቀበሯት በኋላ በሦስተኛው ቀን ነሐሴ 16 እመቤታችን ተነሥታ ጌታችን ከመላእክት እና ቅዱሳን ጋር ሆኖ ሐዋርያትን አቁርቧቸዋል።(ውዳሴ ማርያም ትርጉም)።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምሮ እና ሐዋርያት መሠረት ላይ የታነፀችው ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን የሐዋርያትን ግብር ምሳሌ በማድረግ ልክ እንደ ሐዋርያት ለሐዋርያት የተገለጠ በረከት እና የእመቤታችን ረድኤት እንዲያድርብን እንጾመዋለን።በቤተ ክርስቲያናችን ከአምስቱ የአዋጅ አጽዋማት መካከልም በመሆኑም ሁሉም ምእመናን እንዲጾም ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች። ነቢዩ ዳንኤል በትንቢተ ዳንኤል ምዕ 10፣21 ላይ እንደተጠቀሰው ”በዚያም ወራት እኔ ዳንኤል ሦስት ሳምንት ሙሉ ሳዝን ነበርሁ።ማለፊያ እንጀራም አልበላሁም፥ ሥጋና ጠጅም በአፌ አልገባም፥ ሦስቱም ሳምንት እስኪፈጸም ድረስ ዘይት አልተቀባሁም።” እንዳለ ጾሙን ከፅሉላት ምግቦች ከሥጋ እና ወተት ውጤቶች በመጾም እና ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሔድ፣በስግደት፣በምፅዋት እና በጾሎት ይጾሙታል።

የእግዚአብሔር ቸርነት የእመቤታችን ድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን!

በኖርዌይ የኢትዮጵያ ኦ/ተዋህዶ ኦስሎ ቅዱስ ገብርኤል፣አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤ/ክርስቲያን
ስብከተ ወንጌል ክፍል