መፃጉዕ (የዐቢይ ጾም አራተኛ ሳምንት)

ቅዱስ ያሬድ የዐቢይ ጾምን በሰየመበት አጽዋማት ላይ አራተኛው ሳምንት መፃጉዕ በመባል ይታወቃል፡፡መፃጉዕ ማለት ትርጓሜው በቁሙ ሲፈታ “ጐባጣ” ማለት እንደሆነ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ ላይ ፈትተውታል፡፡

መፃጉዕ የስያሜው ዋና ታሪክ፥በኢየሩሳሌምም በበጎች በር አጠገብ በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ በምትባልና አምስትም መመላለሻ በነበረባት አንዲት መጠመቂያ ሥፍራ ከሠላሳ ስምንት ዓመት ጀምሮ ስለታመመ አንድ ሰው የሚተርክ ነው፡፡ ጌታ ወደዚህ ሥፍራ የመጣው በሰንበት ቀን ነው፡፡ በዚያም የመጠመቂያውን ቦታ ውኃ የእግዚአብሔር መልአክ ባንቀሳቀሰው ጊዜ ቀድሞ በመግባት ለመፈወስ ወደ ውኃው ይሄዱ ነበር።

የታሪኩ ሙሉ መልዕክት በዮሐንስ ወንጌል ም 5 1-15 ላይ እንዲህ ይነበባል : –

ከዚህ በኋላ የአይሁድ በዓል ነበረ፥ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። በኢየሩሳሌምም በበጎች በር አጠገብ በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ የምትባል አንዲት መጠመቂያ ነበረች፤ አምስትም መመላለሻ ነበረባት።በእነዚህ ውስጥ የውኃውን መንቀሳቀስ እየጠበቁ በሽተኞችና ዕውሮች አንካሶችም ሰውነታቸውም የሰለለ ብዙ ሕዝብ ይተኙ ነበር።አንዳንድ ጊዜ የጌታ መልአክ ወደ መጠመቂያይቱ ወርዶ ውኃውን ያናውጥ ነበርና፤ እንግዲህ ከውኃው መናወጥ በኋላ በመጀመሪያ የገባ ከማናቸው ካለበት ደዌ ጤናማ ይሆን ነበር።በዚያም ከሠላሳ ስምንት ዓመት ጀምሮ የታመመ አንድ ሰው ነበረ፤ ኢየሱስ ይህን ሰው ተኝቶ ባየ ጊዜ፥ እስከ አሁን ብዙ ዘመን እንዲሁ እንደ ነበረ አውቆ። ልትድን ትወዳለህን? አለው።ድውዩምጌታ ሆይ፥ ውኃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያይቱ ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም ነገር ግን እኔ ስመጣ ሳለሁ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል ብሎ መለሰለት።ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለው። ወዲያውም ሰውዬው ዳነ አልጋውንም ተሸክሞ ሄደ።ያም ቀን ሰንበት ነበረ። ስለዚህ አይሁድ የተፈወሰውን ሰው። ሰንበት ነው አልጋህንም ልትሸከም አልተፈቀደልህም አሉት።እርሱ ግን፦ ያዳነኝ ያ ሰው። አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለኝ ብሎ መለሰላቸው።እርሱም፦ አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ያለህ ሰው ማን ነው? ብለው ጠየቁት።ዳሩ ግን በዚያ ስፍራ ሕዝብ ስለ ነበሩ ኢየሱስ ፈቀቅ ብሎ ነበርና የተፈወሰው ሰው ማን እንደ ሆነ አላወቀም።ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በመቅደስ አገኘውና። እነሆ፥ ድነሃል፤ ከዚህ የሚብስ እንዳይደርስብህ ወደ ፊት ኃጢአት አትሥራ አለው።ሰውዬው ሄዶ ያዳነው ኢየሱስ እንደ ሆነ ለአይሁድ ነገረ።

ምንባባት መልዕክታት

(ገላ. 5÷1-ፍጻሜ ምዕ.) እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ፤ እንደገናም በባርነት ቀንበር አትኑሩ፡፡እነሆ÷እኔ ጳውሎስ እላችኋለሁ፤ “ብትገዘሩም በክርስቶስ ዘንድ ምንምአይጠቅማችሁም፡፡” ……

(ያዕ.5÷14- ፍጻሜ ምዕ.) ከእናንተ የታመመ ሰው ቢኖር በቤተ ክርስቲያን ያሉቀሳውስትን ይጥራና ይጸልዩለት፤ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተጸለየበትንም ዘይት ይቀቡት፡፡ …….

ግብረ ሐዋርያት

(የሐዋ.3÷1-11) ጴጥሮስና ዮሐንስም በዘጠኝ ሰዓት ለጸሎት በአንድነት ወደ ቤተመቅደስ ወጡ፡፡ ከእናቱ ማኅፀንም ጀምሮ እግሩ ሽባ ሆኖ የተወለደ አንድ ሰው ነበር፤ ወደመቅደስም ከሚገቡት ምጽዋት ይለምን ዘንድ ሁል ጊዜ እየተሸከሙ መልካም በሚልዋትበመቅደስ ደጃፍ ያስቀምጡት ነበር፡፡(ተጨማሪ ያንብቡ)

ምስባክ

(መዝ.40÷3)እግዚአብሔር ይረድኦ ውስተ ዐራተ ሕማሙ፡፡ ወይመይጥ ሎቱ ኩሎምስካቢ ሁ እምደዌሁ አንሰ እቤ እግዚኦ ተሣሃለኒ

ትርጉም፦ እግዚአብሔር በደዌው አልጋ ሳለ ይረዳዋል፤ መኝታውንም ሁሉ ከበሽታውየተነሣ ይለውጥለታል፡፡

ወንጌል

(ዮሐ. 5÷1-24) ከዚህም በኋላ በአይሁድ በዓል እንዲህ ሆነ፤ ጌታችን ኢየሱስ ወደኢየሩሳሌም ወጣ፡፡ በኢየሩሳሌምም በበጎች በር አጠገብ መጠመቂያ ነበረች፤ ስምዋንምበዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ ይሉአታል፤ አምስት እርከኖችም ነበሩአት፡፡ (ተጨማሪ ያንብቡ)

ቅዳሴ: – ቅዳሴ ዘእግዚእነ

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡