አሠራራችን

በእያመቱ ዓመታዊ ዕቅድና በጀታችንን አዘጋጅተን ለጠቅላላ መንፈሳዊ ጉባዔው በመጨረሻም ለሀገረስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ለብፁዕ አቡነ ኤልያስ እያቀረብንና እያጸደቅን እንሠራለን።  በዓመት ፪ ጊዜ ማለትም በየ ፮ ወሩ ለጠቅላላ ጉባዔው እንዲሁም ለሀገረስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ለብፁዕ አቡነ ኤልያስ የሥራ ክንውንና የሂሳብ ሪፖርት እናቀርባለን። ከላይ የተጠቀሱት የአገልግሎት ክፍሎች ዓመታዊ ዕቅዳቸውን እና የሥራ ክንወን ሪፖርታቸውን በወቅቱ ለሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባዔው እንዲያቀርቡ እየተደረገ ተጠቃሎ እና ተጭምቆ ለበላይ አጽዳቂ ክፍሎች እዲቀርብ እየተደረገ የአፈጻጸም እንቅሥቃሴው ይካሄዳል።

የቤተ-ክርስቲያናችን ርእይ

ከተለመደው «ራእይ» ከሚለው ይልቅ «ርእይ» የሚለው ቢለመድ ከትርጉሙና ለመለት ከፈለግነው አንፃር ተስማሚ ይሆናል። ርእይ ትርጉሙ፦ ማሰብ፣ መመኘት፣ መገምገም፣ መገመት፣ … ማሟረት፣ ትንቢት መናገርና መላ መምታት ማለት ነው። በዓይነ ልብ የሚታይ ሕልማዊ መልክ አለው። «ራእይ» ደግሞ መልክ፣ ፊት፣ ቅርፅ እና ገጽ ዓይነ ሥጋ የሚያርፍበት ማለት ነው። አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መ///ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ (ገጽ ፰፻፲፮)

ስለዚህ ከዚሀ በታች ለማስተዋወቅ ለፈልግነው ሀሳብ የሚስማማው «ርእይ» የሚለው ቃል ነው። ዘመናውያን የውስጥና የውጭ ምሑራን «ርእይ»ን በያባባላቸው ገልጸውታል። ከነሱም አንዱ «ግልጽ የሆነ የሩቅ ጊዜ እይታ /Vision/ የመንደፍ ችሎታ» ብለውታል። ሌላውም ደግሞ «ርእይ» ማለት «አርቆ ማየት» ማለት ነው ያሉ ሲሆን ባለ «ርእይ» መሆን ማለት ደግሞ የዛሬውን ብቻ ሳይሆን ስለ ወደፊቱ ማሰብ፣ ስለ ወደፊቱ ቀድሞ ማየት ወይም ሌሎች ማየት የማይችሉትን መየት የሚችል አይታና ተመልካች ማለት ነው ብለውታል፡፡

ከዚህ በመቀጠል የቤተ-ክርስቲያናችንን ርእይ (Vision) እናስተዋወቃለን

ርእያችን በአንድ ዐረፍተነገር ሲገለጽ፦ በማንኛውም መንገድ በብቃቱና በጥራቱ ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን ቤተክርስቲያን መገንባት።

ርእዩ ሲበተን ወይም ሲዘረዘር

/ ሥርዓተ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶን የጠበቀ የራስ ሕንፃ ቤተክርስቲያን መገንባት።

/ በሥነምግባር የታንፁ፣ በቅድስና ያሸበረቁ፣ መንግሥተሰማያትን የሚናፍቁ፣ በተፈለጉበት የአገልግሎት ዘርፍ ውጤታማ የሚሆኑ ቅንነት፣ብቃትና ታማኝነት ያላቸው መንፈሳውያን አባላትን ማፍራት።

/ መንፈሳዊ ጋዜጣና መጽሔት ማተምና አባላቱን በሚገባ የሚያስተናገድ ጽሕፈት ቤት ማደራጀት።

/ ለአባላቱና ለሌሎችም እንግዳ ደራሽ ባይታወር ለሆኑ መረዳት የሚገባቸው አካላት አገልግሎት መስጠት የሚችሉ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት መስጫ እንደ ክሊኒክ፣ መዋዕለሕፃናትና በጎ አድራጎት ያሉ ተቋማትን በቤተክርስቲያን ሥር ተቋቁመው ማየት።

/ ኖሮጂያንና ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ ኦ//ቤተክርስቲያን ዶግማና ቀኖና ተዛምደውና ተፋቅረው በሁሉም ማዕርግ አብረው ሲያመልኩ፣ ሲያገለግሉና ሲገለገሉ ማየት።

/ በኖርዌይ በኩል ወይም ከእነሡ ጋር ደግሞ መላ አውሮፓን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ማድረግ።

/ ቤተክርስቲያናችን አድጎ የረድዮና ቴሌቪዢን ጣቢያዎችን ተጠቅሞ ወንጌልን ለመላው ዓለም ሲሰብክ ማየት።

/ በዚህ ሀገር የተወለዱትን ወጣቶች ሃይማኖታቸውን፣ ባህላቸውን፣ ቋንቋቸውን፣ ታሪካቸውንና ቤተክርስቲያናቸውን ለመረክብ በቅተውና ነቅተው ማየት።

/ ከሌሎች ጎራ የተቀላቀሉ የቤተክርስቲያን ልጆችን ወደ ሕፅኗ ተመልሰው ማየት።

/ ለሕፃናት፣ ለታዳጌ ወጣቶች፣ ለጎልማሶችና ዐረጋውያን ጥያቄያቸውን በትክክል መመለስ የሚችሉ በእድሜያቸው ተመጣጣኝ የሆኑ መንፈሳዊ ትምህርቶች በበቂ ሁኔታ ተዘጋጅተው ማየት።

/ ከኢትዮጵያ ወጥተው በመንፈስም ሆነ በአቅም ደክመው ተስፋ ከመቁረጥ የሚደርሱትን፣ ቋንቋ ባለማወቅ፣ አማካሪ በማጣት፣ በባይታወርነት የሚቸገሩትን፣ ኢትዮጳያውያን በተለይም ኦርቶዶክሳውያን እንዲሁም ፈቃድ አግኝተው ሲኖሩ እንደ መለያየት፣ የልጅ መቀማት ዐይነት ችግር የሚገጥማቸውን አባላት ጭንቀትና ብስጭት የሚያቃልል ሲታመሙ እንደ ሕመሙ አይነት ምክርና ርዳታ ሊሰጡ ከሚችሉ አካላት ጋር የሚያገናኝ፣ ከሕግም አንፃር መብታቸውን የሚያሳውቅ የሕግና የምክር መንፈሳዊ ክፍል ተቋቁሞ ወገኖቻችንን ወደሌላ ሃይማኖት ከመኮብለል፣ ከጭንቀትና አንገት ከመድፋት ከትካዜ ሲያድን ማየት።

/ የራስ ሕንፃ ቤተክርስቲያን ገንብቶ የሕንፃ ቤ/ክ ቡራኬ /ምርቃት /ሥነሥርዓት፣ ከአውሮፓ መንፈሳዊ ጉባዔ ጋር በማቀናጀት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ወፓትሪያሪክ ዘ ኢትዮጵያ ከአበው ሊቃነ ጳጳሳት ጋር የሚገኙበት፣ ቤተክርስቲያናችንን በኖርዌና በአካባቢ ሀገሮች ሊያስተዋውቅ የሚችል ሚዲያዎችን የሳበ ታላቅና ልዩ መንፈሳዊ በዓልና ጉባዔ ማድረግ። የሚሉት ናቸው።

አንዳንዶቹ ሪያሊስቲክ ናቸው ወይ የሚል ጥያቄ ሊያጭሩ እንደሚችሉ ይገመታል። ሰው ለራሱ ዝና፣ ምስጋና፣ ወይም ለልዩ ልዩ የግል ጥቅም ሳያስብ ለፈጣሪው ክብር፣ ለሀገር፣ለወገን፣ ለሃይማኖትና ለታሪክ ብሎ በቅንነት ከተንቀሳቀሰ ጀማሪውምና ፈጻሚውም ልብንና ኩላሊትን የሚመረምር እግዚአብሔር ስለሆነ ቤተክርስቲያናችን የምትመላለስበት የወደፊት የሥራ አቅጣጭዋ መሠረት አድርጋ ይዛዋለች አምናበታለችም።

የየዓመቱን ዕቅዳችንንም ሆነ ይህን ርእያችንን እውን ለማድረግ በምናደርገው እንቅስቃሴ በሙያ፣በሀሳብ፣በምክር፣ በገንዘብና በጉልበት በተቻላችሁ ሁሉ ከጎናችን እንድትቆሙ ይህንን ለመተመለከቱ ኦርቶዶክሳውያን ወገኖቻችን ሁሉ በኖርዌ ኦስሎ የምትገኘው የቅዱስ ገብርልና አቡነ ተክለ ሃይማኖት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችን ጥሪያዋ ታስተላልፋለች።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን