ቂርቆስ ወኢየሉጣ

“የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፥ ያድናቸውማል።” መዝ(33፡7) ይህ ጥቅስ የእግዚአብሔር መልአክ እግዚአብሔርን የሚፈሩትን ሰዎች ከእግዚአብሔር ተልኮ በዙሪያቸው ሆኖ ከመከራ እንደሚያድናቸው ያስተምራል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በ(ዕብ 1፥14)“ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ ስላላቸው ለማገዝ የሚላኩ የሚያገለግሉም መናፍስት አይደሉምን? ” እንዳለ፤ የመላእክት አንዱ ተግባር መዳንን ይወርሱ ዘንድ ያላቸውን ሰዎች መጠበቅ መሆኑ ይነግረናል፡፡ ከእግዚአብሔር እየተላኩ ለሰው ልጆች ወይም ቅዱሳን ይሆኑ ዘንድ ለተጠሩትና፣ ለእግዚአብሔር በመገዛታቸው ምክንያት ከክፉ ነገርና ከመከራም ከሚታደጋቸው መልአክት መካከል አንዱ ሊቀ መለአክ ቅዱስ ገብርኤል ነው። በመጽሐፈ ስንክሳር፣ በድርሳነ ገብርኤል እና በገድለ ቂርቆስ ወኢየሉጣ እንደ ተመዘገበው ሐምሌ ፲፱ ቀን ቅዱስ ቂርቆስ እና ቅድስት ኢየሉጣ በሰማዕትነት መከራ የተቀበሉበት፤ ስማቸውን የሚጠሩ፣ ዝክራቸውንም የሚዘክሩ ምእመናን ይቅርታን፣ ምሕረትን እንደሚያገኙ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእነዚህ ቅዱሳን ቃል ኪዳን የሰጠበት ቀን ነው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልኮ የተራዳቸውም በዚሁ ዕለት ነው፡፡

የሰማዕታቱ ቅዱስ ቂርቆስንና ቅድስት ኢየሉጣን ገድል እንደሚነግረን ቅድስት ኢየሉጣ በሮም ግዛት በሚገኝ አንጌቤን በሚባል አገር በፈሪሃ እግዚአብሔር፣ በክርስትና ሃይማኖት እና በበጎ ምግባር ጸንታ ትኖር የነበረች ደግ ሴት ናት፡፡ በሥርዓት ያሳደገችው ቂርቆስ የሚባል ሕፃን ልጅም ነበራት፡፡ ይህቺ ቅድስት የዘመኑን አረማዊ መኰንን እለእስክንድሮስን በመፍራቷ ከልጇ ጋር ከሮም ወደ ጠርሴስ በተሰደደች ጊዜ መኰንኑ እነርሱ ከሚገኙበት አገር ገብቶ ክርስቲያኖችን እያሳደደ መግደል ጀመረ፡፡ የንጉሡ ወታደሮችም እግዚአብሔርን እንዲክዱ፤ ለጣዖት እንዲሰግዱ ቅድስት ኢየሉጣንና ቅዱስ ቂርቆስን አስፈራሯቸው፡፡ ቅዱሳኑ ግን ለጣዖቱ ለመስግድና ሃይማኖታቸውን ለመለወጥ ፈቃደኛ አልኾኑም ነበር፡፡ በዚህም መኰንኑ ተቈጥቶ በዓይንና በአፍንጫቸው ውስጥ ጨውና ሰናፍጭ በመጨመር፤ በጋሉ የብረት ችንካሮች በመቸንከርና መላ ሰውነታቸውን በመብሳት በብዙ ዓይነት መሣሪያ አሠቃያቸው፡፡ እግዚአብሔርም የጋሉ ብረቶችን እንደ ውኀ ያቀዘቅዝላቸው፤ ሥቃያቸውንም ያቀልላቸው ነበር፡፡

በሌላ ጊዜም በገመድ አሳሥሮ ንጉሡ ሲያስጨንቃቸው ከቆየ በኋላ ራሳቸውን ከቆዳቸው ጋር አስላጭቶ እሳት አነደደባቸው፡፡ ዳግመኛም ከትከሻቸው እስከ እግራቸው ድረስ በሚደርሱ ችንካሮች ቸነከራቸው፡፡ በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልኮ ከሥቃያቸው አድኗቸዋል፡፡ አሁንም ቀኑን ሙሉ በልዩ ልዩ የሥቃይ መሣሪያዎች ቢያስጨንቃቸውም የእግዚአብሔር ኃይልና የቅዱስ ገብርኤል ተራዳኢነት አልተለያቸውም ነበርና ምንም ዓይነት ጉዳት አልደረሰባቸውም፡፡ እንደገናም በመጋዝ ሰንጥቀው በብረት ምጣድ በቆሏቸው ጊዜ ጌታችን ከሞት አነሣቸውና በመኰንኑ ፊት ድንቅ ተአምራትን አደረጉ፡፡ ከተአምራቱ መካከልም ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ የመኰንኑን ጫማ በጸሎት ወደ በሬነት እንዲቀየር ማድረጉ ተጠቃሽ ሲኾን፣ መኰንኑ በተአምራቱ ተቈጥቶ የቅዱስ ቂርቆስን ምላስ አስቈርጦታል፤ ጌታችንም ምላሱን አድኖለታል፡፡ ዳግመኛም በፈላ የጋን ውኀ ውስጥ ቅዱሳን ቂርቆስና ኢየሉጣን ሊጨምሯቸው ሲሉ ቅድስት ኢየሉጣ በፈራች ጊዜ ቅዱስ ቂርቆስ እናቴ ሆይ አትፍሪ፤ አናንያ፣ ዓዛርያና ሚሳኤልን ከእሳት  ነበልባል  ያዳናቸው እግዚአብሔር  እኛንም ከዚህ የፈላ ውኀ ያድነናል”  እያለ ያረጋጋትና በተጋድሎዋ እንድትጸና ወደ እግዚአብሔር ይጸልይላት ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ተያይዘው ወደ ጋኑ ውስጥ ገቡ፡፡ ያ ውኀም እንደ ውርጭ ቀዘቀዘ፡፡ ደግሞም ወታደሮቹ መንኰራኵር ባለበት የብረት ምጣድ ውስጥ አስገብተው ሥጋቸው እስኪቈራረጥ ድረስ በጎተቷቸው ጊዜ ከእግዚአብሔርየተላከ  መለአክ ቅዱስ ገብርኤል አድኗቸዋል፡፡ መኮንኑም በታላቅ ስቃይ ያሰቃያቸው ዘንድ አስቦ እስኪመክር ድረስ በወህኒ ቤት ዘጋባቸው። ያንጊዜም ክብር ይግባውና  ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሕፃኑ ቂርቆስ ወርዶ አጽናናው፤ አረጋጋውም፤ ስሙንም ለሚጠራና መታሰቢያውን ለሚያደርግ ቃል ኪዳን ሰጠው።

በመጨረሻም ከእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ተቀብለው በመንፈቀ ሌሊት አንገታቸውን ተቈርጠው በሰማዕትነት ዐርፈዋል፡፡ እስከ ሞት ድረስ በታመኑበት ተጋድሏቸውም ከእግዚአብሔር ዘንድ የሕይወትን አክሊል ተቀብለዋል፡፡ በአጠቃላይ ቅዱስ ቂርቆስና ቅድስት ኢየሉጣ የዚህን ዓለም ጣዕም በመናቅ ”ሞት ቢኾን፣ ሕይወትም ቢኾን፣ መላእክትም ቢኾኑ፣ ግዛትም ቢኾን፣ ያለውም ቢኾን የሚመጣውም ቢኾን፣ ኃይላትም ቢኾኑ፣ ከፍታም ቢኾን፣ ዝቅታም ቢኾን፣ ልዩ ፍጥረትም ቢኾን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ” (ሮሜ. ፰፥፴፰-፴፱) በማለት ቅዱስ ጳውሎስ የተናገረውን ቃል በተግባር በማሳየት ለክርስቶስ ፍቅር ሲሉ ራሳቸውን ለመከራና ለሞት አሳልፈው ሰጥተዋል፡፡ ቅዱሳኑ ተጋድሏቸውን እስኪፈጽሙ ድረስም ቅዱስ ገብርኤል አልተለያቸውም፡፡ በቅዱስ ገብርኤል ተራዳኢነት ቅድስት ኢየሉጣና ቅዱስ ቂርቆስ ብቻ ሳይኾኑ ብዙ ምእመናንም ተጠቅመዋል፡፡ ስሙ በሚጠራባቸው ገዳማትና አድባራት መልአኩ የሚያደርጋቸው ድንቅ ድንቅ ተአምራት ለዚህ ማስረጃዎች ናቸው፡፡ ይህም ከላይ በርዕሱ እንደተገለፀው ቅዱሳን መላእክት በእግዚአብሔር ስም መከራ የሚቀበሉ ምእመናንን እንደሚጠብቁና ከልዩ ልዩ ደዌ እንደሚፈውሱ የሚያስረዳ ታሪክ ነው፡፡

እኛም በሃይማኖታችን ምክንያት መከራ ባጋጠመን ጊዜ ቆራጥ ልብ ያለው ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ  እናቴ ሆይ አትፍሪ”  እያለ እናቱን በመከራ እንድትጸና እንዳረጋጋትና ለሰማዕትነት እንድትበቃ እንዳደረጋት ዅሉ፣ ዘለዓለማዊውን የእግዚአብሔርን መንግሥት በአንድነት ለመውረስ እንድንችል አይዞህአይዞሽአትፍራአትፍሪ”  በመባባል በዚህ ዓለም የሚገጥመንን መከራ ታግሠን፣ እስከ ሞት ድረስ በሃይማኖታችን ጸንተን መኖር ይገባናል፡፡ ክርስትና ለብቻ የሚጸደቅበት መንገድ ሳይኾን በጋራ ዋጋ የሚያገኙበት የድኅነት በር ነውና፡፡ ከዚሁ ዅሉ ጋርም ቅዱስ ቂርቆስንና ቅድስት ኢየሉጣን የተራዳው የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል በአማላጅነቱ እንዲጠብቀን በእግዚአብሔር ታምነን በቀንም በሌሊትም ዘወትር ልንማጸነው ያስፈልጋል፡፡ ”የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙርያ ይሠፍራል፤ ያድናቸውማልተብሎ እንደ ተጻፈ ሊቀ መለአክ ቅዱስ ገብርኤል  ከፈጣሪው ከእግዚአብሔር በተሰጠው ቃል ኪዳን መሠረት ከሚደርስብን ልዩ ልዩ መከራና ሥቃይ ያድነናል። ይህን እንድናደርግም የቅዱሳን ተራዳኢነት አይለየን፡፡ የቅዱስ ገብርኤል፣ ቅድስት ኢየሉጣ እና ቅዱስ ቂርቆስ ጸሎታቸው፣ ምልጃቸው ይጠብቀን፡፡አሜን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!

ምንጭ