በዓለ ጰራቅሊጦስ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

በዓለ ጰራቅሊጦስ ወይም በዓለ ጰንጠቆስጤ ከዘጠኙ የጌታችን ዐበይት በዓላት አንዱ ሲሆን መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት የወረደበትን ቀን የምናስብበት በዓል ነው። ጰራቅሊጦስ፡- ቃሉ የግሪክ ነው። “ጰራቅሊጦስ” የሚለው ቃል ከሦስቱ አካላት አንዱ ለኾነው ለእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ መጠሪያ ስሙ ሲኾን፣ ትርጕሙም መጽንኢ (በእምነት የሚያጸና)፣ መንጽሒ (ከኃጢአት የሚያነጻ)፣ ናዛዚ (ያዘኑትን የሚያረጋጋ)፣ መስተፍስሒ (የተጨነቁትን የሚያስደስት)፣ ከሣቲ (ምስጢርን የሚገልጽ) ማለት ነው፡፡ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም የሚሠራውን ሥራ ከጨረሰ በኋላ ቅዱሳን ሐዋርያትን ወደ አባቴ እሄዳለሁ (አርጋለሁ) ሲላቸው ደነገጡ። አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም መደንገጣቸውን አይቶ  ”ልባችሁ አይደንግጥባችሁ በእግዚአብሔር እመኑ በእኔም እመኑ በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ ማለት በአባቴ ቤት በመንግሥተ ሰማያት ብዙ ማዕርገ ሀብታት አለ” (ዮሐ 14፥1) እንዲሁም ”ወላጆች እንደሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም” (ዮሐ 14፥18) ሲል መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱሳን ሐዋርያትን አጽናንቷቸዋል፡፡

በሉቃ 24፥49 ላይ ደግሞ እንደተጻፈው የሰላም አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ሊያርግ ሲል ቅዱሳን ሐዋርያትን ”እነሆ አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኃይልን እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ” አላቸውና ዐረገ፡፡ ይህን አምላካዊ ቃል መሠረት በማድረግ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካረገ በኋላ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ፲፪ቱ ደቀ መዛሙርት፣ ፸፪ቱ አርድእት፣ ፴፮ቱ ቅዱሳት አንስት በኢየሩሳሌም ከተማ በጽርሐ ጽዮን በማርቆስ እናት በማርያም ቤት ሁሉም በአንድ ልብ ኾነው በጾምና በጸሎት ይተጉ ነበር፡፡ በሚያርግበት ጊዜም ለሐዋርያቱ በገባላቸው ቃል መሠረት ተሰብስበው በአንድነት ሳሉ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአረገ በአሥረኛው ቀን በተነሣ በሃምሳኛው ቀን የጰራቅሊጦስ እለት ጧት በሦስት ሰዓት እንደ ዐውሎ ነፋስ ያለ ድምፅ ድንገት ከሰማይ መጣና የነበሩበትን ቤት ሞላው፡፡ ከዚያም እንደ እሳት የተከፋፈሉ የእሳት ላንቃዎች በኹሉም ላይ ተቀመጡባቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ኹላቸውም መንፈስ ቅዱስን ከተሞሉ በኋላ መንፈስ ቅዱስ ባደላቸው መጠን በየአገሩ ቋንቋዎች ኹሉ መናገር ጀመሩ።(ሐዋ ፪፥፩-፬) ጌታችን መንፈስ ቅዱስን ለሐዋርያት የላከበት ይህ ዐቢይ በዓል ጰራቅሊጦስ ይባላል፡፡

ሐዋርያት በጽርሐ ጽዮን ተሰብስበው ሳሉ መንፈስ ቅዱስ በእሳት አምሳል ወርዶ ሰማያዊ ሀብትን፣ ዕውቀትና ጸጋን አድሏቸዋል፡፡ መንፈስ ቅዱስ ከወረደላቸው በኋላም በአእምሮ ጎልምሰዋል፤ ጥቡዓን (ቈራጦች)፣ ፍርሃት ከውስጣቸው ተወግዶ መንፈሳዊ ድፍረት አግኝተዋል፤  ጽኑዓን ኾነዋል፤ ለስብከተ ወንጌል የሚፋጠኑበትንና ለሰማዕትነት የሚዘጋጁበትን ልቡና ታድለዋል፡፡ ቀድሞ ይናገሩት ከነበሩት ከዕብራይስጥ ቋንቋ በተጨማሪ ፸፩ ቋንቋዎች ተገልጸውላቸው ምሥጢራትን መተርጐም ጀምረዋል፡፡ የአገሩ ሁሉ ቋንቋ የተገለጸላቸውም ሁሉንም በአገሩ ቋንቋ እንዲያስተምሩ ነው፡፡ ከተለያየ ክፍለ ዓለም የመጡ ነበሩ፡፡ እነዚህ የገሊላ ሰዎች አይደሉምን? እንዴት የእኛን አገር ቋንቋ ሊናገሩ ቻሉ? በማለት ተገረሙና አመንትተው እርስ በርሳቸው እንጃ ይህ ምን ይሆን? አሉ፡፡ ከአይሁድ ወገን አንዳንዶቹም ሐዋርያትን “ጉሽ ጠጅ ጠጥተው ሰክረው የኾነ ያልኾነውን ይቀባጥራሉ” ይሏቸው ነበር፡፡

ነገር ግን ቅዱስ ጴጥሮስም ይህንን ሀሳባቸውን በመንፈስ ቅዱስ አውቆ ድምፁንም ከፍ አድርጎ እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፡- የይሁዳ ሰዎች በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሁላችሁ፡- ይህ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን ቃሎቼንም አድምጡ፡፡ ሰክረዋል የምትሉ ለእናንተ እንደመሰላችሁ እነዚህ የሰከሩ አይደለም፡፡ ጊዜው ማለዳ፣ ሰዓቱም ገና ሦስት ሰዓት ነውና፡፡ ዳሩ ግን በነቢዩ ኢዩኤል ”እግዚአብሔር ይላል በኋለኛይቱ ቀን እንዲህ ይሆናል ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ ጎበዞቻችሁም ራእይ ያያሉ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልም ያልማሉ ደግሞም በዚያች ወራት በወንዶችና በሴቶች አገልጋዮች ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ ትንቢትም ይናገራሉ፡፡ ድንቆችንም በላይ በሰማይ ምልክቶችንም በታች በምድር ደምም፣ እሳትም የጢስ ጭጋግም ይሆናል የታወቀችዋም ታላቅዋ የእግዚአብሔር ቀን ሳትመጣ ፀሐይ ወደ ጨለማ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣል የእግዚአብሔርን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል” (ኢዩ 2፥28-32) ተብሎ የተነገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ይህንን ድንቅ ተአምር ያደረገው እናንተ የሰቀላችሁት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ በማለት ሐዋርያት ኢየሱስ ክርስቶስ ነቢያት ትንቢት የተናገሩለት፣ ምሳሌ የመሰሉለት አምላክ ወልደ አምላክ መኾኑን፣ ከሙታን ተለይቶ መነሣቱን፣ ማረጉንና ዳግም በክብር በምስጋና መጥቶ በሕያዋንና በሙታን ላይ የሚፈረድ መኾኑን እንደሚመሰክሩ በአይሁድ ፊት ልብን የሚነካ ትምህርት ሰጠ፡፡

በቅዱስ ጴጥሮስ ትምህርት የተማረኩ አሕዛብም ቅዱስ ጴጥሮስንና ሌሎቹንም ሐዋርያት ወንድሞች ሆይ ምን እናድርግ? አሉአቸው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም ንስሐ ግቡ ኃጢአታችሁም ይሠረይ ዘንድ ተጠመቁ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ፡፡ የተስፋው ቃል ለእናንተና ለልጆቻችሁ አምላካችንም ወደ እርሱ ለሚጠራቸው በሩቅ ላሉ ሁሉ ነው፤ ስለዚህ ራሳችሁን ከዚህ ክፉ ዓለም አድኑ ብሎ መከራቸው፡፡ በዚህ ቀን ሦስት ሺህ ሰዎች አምነው ተጠመቁ፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው የሞቱና የትንሣኤው ምስክሮች ሆኑ፡፡ ሐዋ.፪፥፩-፵፩) ይህም ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ ከወረደላቸው በኋላ ያደረባቸው የማሳመን ጸጋና ተአምራትን የማድረግ ኃይላቸው እንደ በዛላቸው ያመላክታል፡፡

የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ በነሱ ላይ ሲያድር ለቤተክርስቲያን ጉዞ አዲስ ምዕራፍ ተከፈተ፡፡ ይህ የጰራቅሊጦስ በዓል በግሪኮች ቋንቋ ጰንጠቆስጤ ይባላል፡፡ ጰንጠቆስጤ ማለት ሃምሳኛ ማለት ነው፡፡ ጌታችን ከተነሣ በኋላ ሃምሳኛው ቀን ነው፡፡ ይህም ዕለት በዓለ ሃምሳ፣ በዓለ ጰራቅሊጦስ ነው፡፡ ይህ ዕለት ሀብተ መንፈስ ቅዱስ የተሰጠበት፤ ብዙ ሺሕ ምእመናን የተገኙበት ዕለት በመኾኑ ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህን በዓል በሚገባ አነጋገር ”የቤተክርስቲያን የልደት ቀን” ብሎታል፡፡ ይህ በዓል በብሉይ ኪዳን የእሸት በዓል (በዓለ ሰዊት) ይባላል፡፡ እስራኤል የነጻነት በዓላቸውን ከሚያከብሩበት ከበዓለ ፋሲካ ጀምረው ሃምሳውን ቀን በዓል አድርገው ይሰነብታሉ፡፡ በሃምሳኛው ቀን በዓለ ሰዊትን (የእሸት በዓላቸውን) ያከብራሉ፡፡ በሀገራቸው ከመጋቢት እስከ ግንቦት ያለው ወቅት በሀገራችን ከመስከረም እስከ ኅዳር እንዳለው የእሸት ወራት (የጸደይ ወራት) ነውና። የእሸት በዓላቸውን የሚያከብሩት በኦሪት ዘሌዋውያን ምዕራፍ 23፥10-17 በታዘዘው መሠረት ማንኛውም እሥራኤላዊ ገበሬ ከዘራው ሁሉ በያይነቱ እሸቱን ቆርጦ ተሸክሞ ወደ ምኩራቡ ይመጣል፡፡ በቤተ መቅደስ የሚያገለግለው ካህን ተቀብሎ ባርኮ ጸልዮ የሚጠበሰው እየተጠበሰ የሚታሸው እየታሸ በማኅበር አንድነት ይበላል፡፡ ይህም ‹‹ቀዳምያት›› ይባላል፡፡ የመጀመሪያው ማለት ነው፡፡ ከማንኛውም በረከት የመጀመሪያው እግዚአብሔር ፊት መቅረብ፣ ለእግዚአብሔር መሰጠት እንዳለበት ታዟልና፡፡

በዚህ መሠረት ከበዓለ ጰራቅሊጦስ የምንማረው፡-ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱሳን ሐዋርያትን ”እናንተ ግን ከላይ ኃይልን እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ” ባላቸው መሠረት በኢየሩሳሌም ቆይተው ተስፋውን ሲጠባበቁ መንፈስ ቅዱስ ወርዶላቸዋል፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት በዚህች ቀን በሦስት ሰዓት ኢየሱስ ክርስቶስ ጰራቅሊጦስን ልኮልናልና በላያችን ኃይልን ሞላ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ በሕያዋንና በሙታን ይፈርድ ዘንድ ሥልጣን እንዳለው በአዲስ ቋንቋ ተናገርን፤ በማለት በዕለቱ ያዩትንና የተደረገላቸውን፣ እንደዚሁም ስለ በዓሉ ታላቅነት ከመሰከሩ በኋላ ይህንን በዓል ማክበር እንደሚገባ አዝዘዋል፤ በአንጻሩ በዚህ ወቅት (በበዓለ ኀምሳ) መጾምና ማዘን ተገቢ አለመኾኑን ተናግረዋል /ዲድስቅልያ ፴፥፴፰-፴፱፤ ፴፩፥፷፱-፸/፡፡

ስለዚህም ዛሬ መንፈስ ቅዱስ የሚወርድባት ኢየሩሳሌም ቤተክርስቲያን ናት። ለዚህም ነው ዘወትር በቅዳሴ መጀመሪያ ላይ ”ይህች ቀን ምን ያህል የምታስፈራ ናት? ይህች ሰዓት ምን  ያህል የምታስጨንቅ ናት? መንፈስ ቅዱስ ከሰማየ ሰማያት የሚወርድባት” የሚባለው። ለቅዱሳን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ እንደ ወረደላቸው ለእኛም እንዲወርድልን ሁልጊዜ ቤተ ክርስቲያን መሄድና መገኘት ይገባል፡፡ ከቤተክርስቲያን ተለይቶ ጽድቅ የለም። ቤተ ክርስቲያን፡- የመንግሥተ ሰማያት በር ናት። በ(ዘፍ 28፥17) “ይህች የሰማይ ደጅ ናት” እንደተባለ። በዚህ መሠረት ለእኛም በ40 ቀንና በሰማንያ ቀን የተሰጠን ጸጋ መንፈስ ቅዱስ እንዳይለየን ሕጉን ትእዛዙን መጠበቅና ጧት ማታ ወደ ቤተ ክርስቲያን መገስገስ ይገባል፡፡

በተጨማሪም ከላይ እንደተገለፀው ቀደምት የቤተክርስቲያን መጻሕፍት እንደሚያስረዱት ቅዱሳን ሐዋርያት ከጌታችን ዕርገት እስከ ኀምሳኛው ቀን ቅድመ ጰራቅሊጦስ (ለ10 ቀናት) ድረስ በጾምና በጸሎት ቆይተዋል፡፡ እነዚህንም 10ቀናት የጾሙት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምድር ላይ እያለ ”እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤  እርሱም ዓለም የማያየውና የማያውቀው ስለ ሆነ ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው…ወላጆች እንደ ሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም”(ዮሐ 14፡16-18) ብሎ የሰጣቸውን ተስፋ እየተጠባበቁ ነበር፡፡ ይህንን ጾም በመጾም ሐዋርያት ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል ራሳቸውን አዘጋጅተውበታል፡፡ ዛሬም ካህናት ክህነት ከመቀበላቸው በፊት፣ አዳዲስ ተጠማቂዎችም ከጥምቀት በፊት እንዲሁም ክርስቲያኖች ሁሉ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ከመቀበላቸው በፊት የሚጾሙት ይህንን አብነት አድርገው ነው፡፡ የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ለመቀበል ራስን በጾምና በጸሎት ማዘጋጀት ያስፈልጋልና፡፡

እንግዲህ ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላም ጾምን የአገልግሎታቸው መጀመሪያ አድርገውታል፡፡ሐዋርያት የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ከተቀበሉ በኋላ (ድኅረ ጰራቅሊጦስ) የጾሙት ስለ ሁለት ዓላማ ነው፡፡ አንደኛው ስለተሰጣቸው ጸጋ መንፈስ ቅዱስ አምላካቸውን ለማመስገን ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ  በዓለሙ ሁሉ ዞረው ለሚሰብኩት ወንጌል ራሳቸውን ለማዘጋጀት ነው፡፡ ስለዚህም ነው መንፈሳዊ አገልግሎትና ስብከት የዚህ ጾም አንኳር ነጥቦች የሆኑት፡፡ ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ ከወረደላቸው በኋላ መጾማቸው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አብነት አድርገው ነው፡፡ እርሱ በማየ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ ሲጠመቅ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ጌትነቱን ለመመስከር ከወረደ በኋላ ሳይውል ሳያድር ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ ሄዶ በዚያ 40 መዓልትና 40 ሌሊት ጾሟልና እነርሱ ደግሞ ኃይል ይሆናቸው ዘንድ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን በበዓለ ጰራቅሊጦስ ዕለት ከተቀበሉ በኋላ ጾምን የሥራቸው ሁሉ መጀመሪያ አድርገዋል፡፡

በዚህም መሠረት የሐዋርያት ጾም የሚጀምረው ከጰራቅሊጦስ ማግስት ዕለተ ሰኞ ጀምሮ ሲሆን ፍፃሜው ደግሞ አብሮ ለማሰብ እንዲረዳ እስከ የቅዱስ ጳውሎስና ቅዱስ ጴጥሮስ በኔሮን ቄሳር በሮም አደባባይ ሰማዕትነት የተቀበሉበትን ዕለት (ሐምሌ 5) ድረስ  ነው ። ስለሆነም ቤተ ክርስቲያን  ልጆቿ የሐዋርያትን በረከትን ያገኙ ዘንድ ከሰባቱ አጿማት አንዱን ጾመ ሐዋርያትን ሁሉም እንዲጾመው አውጃለች። በአጠቃላይ በሐዋርያት ጾም የሐዋርያት ክብራቸውና አገልግሎታቸው ይታሰባል፡፡ ይህን ጾም የምንጾመው የሐዋርያትን በረከት ለመላበስ፣ እነርሱ ድል ያደረጉትን ዓለም እንድናሸንፈው አምላካችንን ለመማጸን ነው፡፡ በዚህ ጾም ሐዋርያት ሁሉን ትተው ጌታን መከተላቸው፣ ዓለምን ዞረው ማስተማራቸውና ስለ ቅዱስ ስሙ በጽናትና በጥብዐት መከራ መቀበላቸው ይዘከራል፡፡ ምዕመናን/ት እና ካህናትም የቅዱሳን ሐዋርያትን መንፈሳዊ ተጋድሎ እያሰብን በዘመኑ ሁሉ በፍቅር በተዋበ የመታዘዝ ፍርሃት የየራሳችንን መዳን እንፈጽም ዘንድ (ፊልጵ. 2፡12) ጾምን በመጾም፣ ጸሎትን በመጸለይ ከእግዚአብሔርና በንፁህ ደሙ ከዋጃት ቅድስት ቤተክርስቲያን ጋር ያለንን ፍጹም አንድነት ልናጸና፣ ራሳችንን ከኃጢአት ከበደል አርቀን በመታዘዝ ጸጋ የጾምን በረከት ልንቀበልበት ይገባል፡፡ ለዚህም የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን አማላጅነት የቅዱሳን ሐዋርያት ጸሎት ይርዳን፡፡ አሜን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!

ምንጭ