አስተርዮ

ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ የልደት ዕለት ከታህሳስ 29 ጀምሮ እስከ ጥር መጨረሻ ያለው ወቅት ዘመነ አስተርዮ ይባላል፡፡ አስተርእዮ ማለት መገለጥ ማለት ነው፡፡የሰው ልጅ አዕምሮ ሊረዳው በሚችለው መጠን የተገለጠው ደግሞ እግዚአብሔር ነው።ከአዳም ጀምሮ እስከ ኖኅ ከዚያም እስከ አብርሃምና ቀጥሎ እስከኖሩት አበው ድረስ እግዚአብሔር በተለያየ መንገድ ተገልጧል።ይህ በቂ ባልሆነም ጊዜ በሙሴ አማካኝነት ሕገ ኦሪትን በመስጠት ለእስራኤል ዘሥጋ በተረዳ መንገድ ተገልጧል።አሁንም ግን ይህ በቂ ስላልሆነ ሰው ወዳጅ የሆነው አምላክ በሥጋ ተገልጦ፣የሰማይን ምስጢር ከፍቶ አሳየን።

በዚህ በዘመነ አስተርዮ ብሉይን ወደ ሐዲስ፣ ዘመነ ፍዳውን ወደ ዘመነ ምሕረት፣ የሚቀይር አንድ ጌታ እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ በኅቱም ድንግልና ያለ አባት በፍጹም ትሕትና ከእናታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ሥጋን ነሳ፡፡ ዘመን የማይቆጠርለት የዘመናት ጌታ እንዲቆጠርለት የማይወሰነው ጌታ ይጨበጥ ይዳሰስ ዘንድ ግድ ሆነ ግድ እንዲሆን ያደረገው እውነተኛ አምላክ ለሰው ልጅ የነበረው ፍቅር ነው፡፡ ‹‹እንዲሁ ወደድኳችሁ›› እንዳለ ‹‹ፍቅር ስሃቦ ለወልድ እመንበሩ›› ብሎ ሊቁ እንደተናገረው በፍጹም ካሳ ከፋይነት ያ ቃል እግዚአብሔር የነበረ ‹‹ቃል ሥጋ ሆነ፤ ጸጋና መንፈስን ተሞልቶ በኛ አደረ››ዮሐ. 114 ‹‹ለዚህ ድንቅ ነገር ምሥጢር አንክሮ ይገባል ድንግል ፈጣሪዋን ወለደችው›› ሃይማኖተ አበው። ይህ ያለንበት ወቅት የፍቅር መጀመሪያው የጥል ግርግዳ የመፍረሻው ዋዜማ ነበር፡፡ ለዚህ ነው መገለጥ የሚባለው እውነተኛ ፍቅር የተገለጠበት ስለሆነ በብሉይ ተሰውሮ የነበረው የአንድነትና የሦስትነት ምሥጢር ተገልጧል፡፡

ሰው በስሜት ህዋሳቱ ቀርፆ በአእምሮው የሚገነዘበው ምድራዊውን ነገር ብቻ ነው።ሰማያዊው ምስጢር የሚታወቀው በሌላ መንፈሳዊ ሕዋስና ከአእምሮ በላይ በሆነ አእምሮ ነው።ይሄውም አእምሮ (ልቦና) እምነት ይባላል።ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ሲገልጥ “እምነት የማናየውን ነገር የሚያስረዳ ነው” ዕብ 111 ብሏል።የእዚህ አይነቱ እውቀት የወዲያኛውን ዓለም የሚያሳይ የሰማይ ደጅ ነው።በ1ኛ ቆሮ 1312 “ምነው ሰማያትን ቀድደህ ብትወርድ” የሚለው የሰው ልጅ የዘመናት ምኞት ምላሽ አግኝቶ በያዝነው በእዚህ ዘመነ አስተርዮ ታይቷል።

አዳምና ሔዋንን ያሳታቸው እባብ ድል የሚነሳበት ዘመን እንደሚመጣ፣ ከሔዋን ዘር የሚገኘው/ የሚወለደው ጌታ የእባቡን ራስ ቀጥቅጦ እንደሚያጠፋው የተነገረበት (ዘፍ315)፣ የእግዚአብሔር ቋንቋ የገባቸው አዳምና ሔዋን ይህንን አምላካዊ ተስፋ በማድረግ የተፈቀደላቸውን ዘመን በየዘመኑ የተነሱ ልጆቻቸውም ይህንን የተስፋ ቃል ሲጠባበቁ እግዚአብሔር እንደገለጸላቸው ስለርሱ ሰው መሆን ትንቢት ሲናገሩ ያንንም ቀን ለማየት ሲመኙ ነበር የኖሩት፡፡ ግን ሳያዩ አለፉ፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ቃል ኪዳኑን የሚጠብቅ፣ የተናገረውን የማይረሳ ነውና የዘመኑ ፍጻሜ ሲደርስ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደ (ገላ44)፡፡አዳም በኃጢአቱ ምክንያት ጸጋው ተገፏል ባሕሪውም ጎስቁሏል ለ7 ዓመት በግልጥ ሲሰማ የነበረውን የአምላኩን ድምፅ እንኳ በኃጢአት ምክንያት መስማት ፈርቶ ‹‹በገነት ድምፅ ሰማሁ ዕራቁቴንም ስለሆንኩ ፈራሁ ተሸሸግሁም›› ዘፍ. 31 ያለበት ዘመን አልፎ ይህ የአስተርዮ (የመገለጥ) ዘመን እርቅ የተጀመረበት፣ ሰው እና መላእክት በአንድ ቋንቋ የዘመሩበት፣ የእዳ ደብዳቤ የተደመሰሰበት፣ የሦስትነትን የአንድነትን ምሥጢር በግልጥ የታወቀበትና የነቢያት ትንቢታቸው ተስፋቸው የተፈጸመበት ወቅት ስለሆነ ቤተክርስቲያናችን የመገለጥ ዘመን ትለዋለች፡፡

አስተርዮ (የእግዚአብሔርን መገለጥ) ቀድሞ አብርሃምን ያነጋገረ አምላክ ለሙሴም በደብረሲና እንደተገለጠ በልዩ ሦስትነቱ ለማያውቁት እግዚአብሔር አብ በሰማይ የምወደው ልጄ ይህ ነው ብሎ እየመሰከረ፣እግዚአብሔር ወልድ በዮርዳኖስ ወንዝ በመጥምቀ ዮሐንስ እጅ ሲጠመቅ እና እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳያ ሲወርድ በግልጥ ታይቷል። (ማቴ፣316)።ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ ሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር በዚህ ዓለም ኖሮ ሥራ ከሠራባቸው ዕለታት ከፍተኛ ምሥጢር የተገለጸበት ዕለት አንዱና ዋነኛው የጥምቀት ዕለት ነው፡፡

በሌላ በኩል ዘመነ አስተርዮ ሲነሳ በጥር 21 የሚከበረው “አስተርዮ ማርያም” ማንሳት ተገቢ ነው።ይህ ቀን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በምድር ላይ የኖረችባቸውን ስልሳአራት ዓመታት ኖራ ያረፈችበት ዕለት ነው። “እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ፥ እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፥ ይኸውም ዲያብሎስ ነው፥በሕይወታቸው ሁሉ ስለሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ፥ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ፡፡ የአብርሃምን ዘር ይዟል እንጂ የያዘው የመላእክትን አይደለም” ዕብ214-15/ እንዳለ፣የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እረፍት በራሱ የአዳም ዘር መሆኗን አስረግጦ ነግሮናል፡፡እመቤታችን በእግዚአብሔር ፍቃድ ብታርፍም ሥጋዋ በምድር አልቀረም እንደልጅዋ አርጋለችና።

ቅዱስ ያሬድ እንዳለው ጌታችን በፍርዱ አድልዎ የሌለበት መሆኑ ይታወቅ ዘንድ እመቤታችን በጥር 21 ቀን አረፈች፡፡ ሥጋ የለበሰ ሁሉ በለበሰው ሥጋ ሞትን ይቀምስ ዘንድ የግድ ነውና፡፡ ትንሣኤ በቃል መነገሩ በአንደበት መዘከሩ ለአምላካችን ለልዑል እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይግባውና “ከሞት ወጥመድ በላይ እንኳን የሆነ ሌላ ኃይል አለ፤ ይሄውም ሞት ፈጽሞ ሊያሸንፈውና ሊገዳደረው የማይችል የእግዚአብሔር መለኮታዊ ኃይል ነው፡፡ በሰይጣን ዘንድ ያለው የሞት ኃይል ነው። ሕያው እግዚአብሔር የሕያዋን አምላክ ነውና ሞት ሊያሸንፈው ሊደርስበትም የማይችለውን ሕይወት ይሰጣል፡፡ ይህንን እግዚአብሔር የሚሰጠውን ሕይወት ሰይጣን በእጁ ሊነካው ከቶውንም አይችልም፡፡ እግዚአብሔር ለሙታን ሕይወትን ይሰጣል የሞትና የሕይወት ባለቤት ነው፡፡” ከሞት ሥልጣንና ኃይል በላይ የሆነው ይኸው የእግዚአብሔር መለኮታዊ ሥልጣን የድንግል ማርያምን ሥጋ መልካምም ሆነ ክፉ ለሠሩ ሰዎች ዋጋ ይከፍል ዘንድ ለፍርድ እስከሚመጣበት ጊዜ ድረስ በመቃብር ውስጥ ተጠብቆ እንዲቆይ፤ ፈርሶና በስብሶ በምድር ላይ እንዲቀር አላደረገም፡፡ከሞቷ ተከትሎ እንድታርግ አደረገ እንጂ።

ባጠቃላይ ዘመነ አስተርዮ የአምላክ በሥጋ የመገለጡን ዘመን የሚዘክርበት ዘመን ነው።ይሄውም በቤተልሄም መወለዱ እና በጥምቀቱ ደግሞ አንድነቱን እና ሦስትነቱን የገለጠበት ዘመን በመሆኑ ነው።ይህ የተገለጠው ስጋ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ስጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ በተዋሕዶ ሰው በመሆን ነው።በዘመነ አስተርዮ መገለጡ በዘመነ ኦሪት ከነበረው ይለያል።በዘመነ ኦሪት የተገለጠው በመለኮታዊ እሳት አምሳል ስለነበር ማንም አይቀርበው ነበር።በዘመነ አስተርዮ ግን ሕዝብ እና አሕዛብ የሚያዩት እና የሚዳስሱት ሆኖ በአጭር ቁመት፣በጠባብ ደረት ተወስኖ የሰው አዕምሮ ሊረዳው በሚችለው መጠን ተገልጧል።

+++++++++++++++++++++///////++++++++++++++++++