ዘወረደ (የዐቢይ ጾም ፩ኛ ሳምንት)

በዐቢይ ጾም ውስጥ ያሉት ሳምንታት ስምንት ስያሜዎች አሏቸው።እነርሱም ዘወረደ፣ቅድስት፣ምኩራብ፣መፃጉዕ፣ደብረዘይት፣ ገብር ኄር፣ኒቆዲሞስ እና ሆሣዕና ናቸው።የዐቢይ ጾም የመጀመርያው ሳምንት ዘወረደ ይባላል።ዘወረደ ማለት ትርጕሙ ‹ከሰማየ ሰማያት የወረደ› ማለት ነው፡፡ ከሰማየ ሰማያት የወረደውን፣ ከድንግል ማርያም የተወለደውን በጥንት ስሙ ወልድ፣ ቃል በኋላ ስሙ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ አማኑኤል የተባለውን ሰው የኾነውን አምላክ ለማመስገን ርደቱን (ከሰማየ ሰማያት መውረዱን) ለመዘከር የሚጾም ጾም ነው፡፡ ጌታችን ጾመ ከማለት አስቀድሞ ከሰማየ ሰማያት መውረዱን ከድንግል ማርያም መወለዱን መናገር አስፈላጊ ነውና የመጀመሪያው ሳምንት ‹ዘወረደ› ተብሏል፡፡ ‹‹አንተ በሰማይ ወአንተ በምድር ወአንተ በባሕር ወአንተ በየብስ» አንተ በሰማይ አለህ፤ በምድር በባሕርም በየብስም አለህ፤›› የተባለውን በሰማይ በምድር ምሉዕ የኾነውን አምላክ ‹ወረደ፤ መጣ› ብሎ መናገር ‹ሰው ኾነ› ማለት ነው፡፡ሰው ኾኖ መገለጡን ለማስረዳት ነው እንጂ መውረድ መውጣት የሚባሉ ቃላት በዅሉ ምሉዕ ለኾነው መለኮት አይስማሙትም፡፡ ቃላቱ ሰውኛ አነጋገርን የሚያመለክቱ ናቸውና፡፡ መተርጕማን አበው ‹‹‹ዘወረደ› ማለት ‹ሰው የኾነ› ማለት ነው›› ብለው ይተረጕማሉ፡፡ አምላካችን ሰው ከኾነ በኋላ ‹መጣ፤ ሔደ፤ ወረደ፤ ዐረገ› የሚሉ ቃላት ይስማሙታል፡፡ ምልዓቱን ሳይለቅ በሰው አካል ተወስኖ ታይቷልና፡፡ ስለዚህ ‹ወረደ› እግዚአብሔር ሰው ኾኖ መገለጡን፤ ‹ዐረገ› ደግሞ የሰውነቱን ሥራ መፈጸሙን ያሳያል፡፡ ዐረገ ስንልም ቀድሞ በሰማይ የለም ለማለት አይደለም፤ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመለኮቱ በዓለሙ ዅሉ ምሉዕ ነውና፡፡

ይህ የመጀመሪያው ሳምንት ጾመ ሕርቃልም ይባላል፡፡ በ714 ዓ.ም.ሕርቃል / ኤራቅሊየስ/ የቤዛንታይን ንጉሥ ነበረ፡፡ይህ ሳምንት በስሙ የተጠራበት ምክንያት በዘመኑ ፋርሶች ኢየሩሳሌምን ወርረው የጌታችን መስቀል ማርከው ወስደው ነበር፡፡ እርሱ ወደፋርስ ዘመቶ መስቀሉን ከእነርሱ ነጥቆ ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሷል፡፡ ሕርቃል ከፋርሶች ጋር ከመዋጋቱ በፊት ሐዋርያት በሲኖዶሳቸው ነፍስ የገደለ ሰው እስከ እድሜ ልኩ ይጹም ብለው ሥርዓት ሠርተዋልና ጾሙን ፈርቶ ስለነበር በኢየሩሳሌም የነበሩ ምእመናን አሳቡ ደግፈው “አንተ ጠላታችንን አጥፋልን ፣መስቀሉን አስመልስልን እንጂ የአንድ ሰው እድሜ ቢበዛ ሰባ ሰማንያ ነው ፡፡ጾሙን አምስት አምስት ቀን ተከፋፍለን እኛ ተከፋፍለን እንጾምልሃለን፡፡”ብለው ጾመውለታል፡፡ይህንን መሠረት በማድረግ ያላወቁት አንድ ጊዜ ጾመው ትተውታል፡፡ ያወቁት ግን ቀድሞም ሐዋርያት ጾመውታል ብለው ሥርዓት አድርገው በዓመት በዐቢይ ጾም መጀመሪያ ላይ ጾመ ሕርቃል ያሉ የሚጾሙት ሆነዋል፡፡ስለዚህ ቤተክርስቲያናችን ይህንን መሠረት በማድረግ በጌታችን ከመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጾም የመጀመሪያውን ሳምንት ጾመ ሕርቃል በሚል ስያሜ እንዲጾም አድርጋለች፡፡ /መጋቢት 10 ስንክሳር ይመልከቱ፡፡/

የቤተ ክርስቲያናችን ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ፣ በዘወረደ ጾመ ድጓው ሰንበት ለሰው ልጆች ብቻ ሳይሆን፣ ሕይወት ላለው ነገር ሁሉ ጸጥታና ሰላም የሰፈነባት የዕረፍት ቀን ስለመሆኗ “አዘዞ እግዚአብሔር ለሙሴ ወይቤሎ ሰብዕከ ወላህምከ ወኲሉ ቤትከ ያዕርፍ በሰንበት” ዘፀ.20፥10፣23፣12፣ ጾመ ድጓ፣ እግዚአብሔር ሙሴን ሕዝብህ የከብትህ መንጋህ ቤተሰብህ ሀሉ በሰንበት ቀን ከድካማቸው ይረፉ በማለት አዘዘው ይላል፡፡ በዚህም ዘመነ ጾም፣ ወይም ጾመ ሙሴ ይባላል፡፡ በጾመ ድጓው ዘወረደ እየተባለ የሚታወቀው፣ በጾመ አርባው ወቅት በተለይም በመጀመሪያው ሳምንት የሚገኘው ያሬዳዊ ድርሰት በነግህ በሠለስት፣ በቀትርና በሠርክ እንዲሁም ቅዳሜና እሑድ በሌሊት የሚዘመር ነው፡፡ በውስጡም የያዘው ፍሬ አሳብ፣ የጾምን፣ የጸሎትን፣ የምጽዋትንና የፍቅርን ጠቃሚነት አጉልቶ የሚያስተምር ነው፡፡ በዚህ በጾም ወቅት በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት በአብዛኛው ከቅዱስ ያሬድ ድርሰቶች ውስጥ የሚዘመረው ምዕራፍ የተባለው ነው፡፡ ምዕራፍ የተባለበት ምክንያትም በየመዝሙራቱ መሀል ሃሌታና ድጓ እያስገባ ለመዝሙሩ ማረፊያ ስላበጀለት በዚህ ምክንያት ምዕራፍ የሚል ስያሜ ሊያገኝ ችሏል፡፡ ይህ የዜማ መጽሐፍ በሁለት ታላላቅ ክፍሎች ይከፈላል፡፡ ይኸውም የዘወትር ምዕራፍና የጾም ምዕራፍ በመባል ይታወቃል፡፡የዘውትር ምዕራፍ የሚባለው በዓመቱ ውስጥ ባሉት ቀናት ውስጥ ሳምንታትና በዓላት ሁል ጊዜ በአገልግሎት ላይ የሚውል ሲሆን፣ የጾም ምዕራፍ የሚባለው ደግሞ በጾመ አርባ ብቻ ለአገልግሎት የሚውል ነው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በዐሥሩ ምህላት አርዕስተ ምህላ በዚሁ ክፍል ይካተታል፡፡ የምዕራፍ ቅንብር ከመዝሙረ ዳዊት፣ ከድጓና ከጾመ ድጓ ጋር የተቀናጀ ነው፡፡ የትምህርት አሰጣጡም እንደ ድጓው ወይም እንደ ዝማሬ መዋሥዕቱ መጽሐፍ ተዘርግቶ ሳይሆን በቃል የሚጠናና የሚወሰን ነው፡፡ ስለሆነም ምዕራፍን ለመማር 150 መዝሙረ ዳዊትን፣ ከነቢያት 15 ምዕራፎችንና 5 መኃልያተ ሰሎሞንን በቃል ሸምድዶ መያዝ ይጠበቅበታል፡፡ ወይም ግድ ነው፡፡ጾምን መጾም የፈቃድ ብቻ ሳይሆን የትእዛዝም ነው፡፡ በዘመነ ብሉይ ነቢዩ ኢዩኤል “ቀድሱ ጾመ ወስብኩ ምህላ” ጾምን ያዙ አጽኑ ምህላንም ዐውጁ ሸማግሌዎቹን ከፈጣሪያችን ቤት ሰብስባችሁ በአንድነት ሁናችሁ ወደ እግዚአብሔር ጩሁ / ለምኑ/ ብሏል፡፡ ኢዮብ ምዕ.1፥11፣ 2፣12፣15-16

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም “በጾም፣ በንጽሐና ተወስናችሁ እግዚአብሔርን አገልግሉ” 2ቆሮ.6፥4-6፡፡ ጾም ከሌለ ወይም ተገቢ ካልሆነ ጌታችን በምትጾሙበት ጊዜ እንደ ግብዞች አትሁኑ ስለ ጽድቅ የሚራቡ የሚጠሙ ንዑዳን ክብራን ናቸው ለምን አለ? ማቴ.5፥፣6፣16፡፡ ነቢዩ ዳዊትም ሰውነቴን በጾም አሳመምኳት በቀጠና፣ በሰልት አደከምኳት ለምን አለ? መዝ.34፥68፣ ት.ዳን.9፥3-4፣ ሐዋርያት ሙሸራውን ከነሱ ለይተው የሚወስዱበት ጊዜ ይመጣል ያን ጊዜ ይጾማሉ ያለውን የጌታን ቃል መሠረት በማድረግ ክርስቶስ በሞት ከተለያቸው በኋላ ጾመዋል፡፡ ጾምንም ሠርተዋል የሐዋ. ሥራ 13፥3፡፡ ሠለስቱ ምዕትም ሐዋርያት የጾሙትንና እንዲጾም የወሰኑትን መጾም ይገባል ብለው ቤተ ክርስቲያን የተቀበለቻቸው አጽዋማት እንዲጾሙ መወሰናቸው ይህን የጌታ ቃል መሠረት በማድረግ ስለሆነ፣ የትእዛዝ መሆኑን ተገንዝበን መጾም አለብን፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሠራዔ ሕግ እንደመሆኑ አርባ ቀን አርባ ሌሊት ጾመ እንጂ እርሱ ሳይጾም ጹሙ አላለንም። ማቴ.4፥2

ምንጭ – ጾምና መንፈሳዊ ሕይወት መጽሐፍ እና

ማ/ቅ ገጽ