በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
«በንተ ኩሉ አጽዋም = ስለ ጾሞች ሁሉ»
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለኢጣሊያና አካባቢው ሀገረ ስብከት ካህናትና መእመናን እንዲሁም ለመላው ኦርቶዶክሳውያን በሙሉ እንኳን ለታላቁ ጾም ለጾመ ኢየሱስ አደረሳችሁ።
መግቢያ
ጾም ማለት ወደ ሰው ከሚገባና ከሰው ከራሱ ከሚወጣ ነገር መከልከል ነው። ወደሰው ከሚገባው ነገር ማለትም በአፍ ከሚገባ ከምግብ እንዲሁም በዓይንና በጆሮ ከሚገቡ የሚያረክሱ ነገሮች በቀኖና በተሥራው ሕግ መሠረት ለተወሰኑ ወራት ወይም ቀናት እስከተወሰነው ሠዓት ድረስ መከልከል ማለት ነው።
በሌላ መልኩ ከውስጣችን ከሚወጡ ነገሮች የምንጾመው ጾም ዐመፀኞች ስለሆን ቢያንስ በአዋጅ አጽዋማት ጊዜ እንኳ እንከልከል ተብሎ ነው እንጂ የዕድሜ ልክ ጾም ነው። እነዚህም ከውስጣችን የሚወጡ የምንከለከላቸው ወይም የምንጾማቸው ነገሮች ምን ምን እንደሆኑ ክብርና ምስጋና ይግባውና ጌታችን እና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ «ወደ አፍ የሚገባ ሁሉ ወደ ሆድ አልፎ ወደ እዳሪ እንዲጣል አትመለከቱምን? ከአፍ የሚወጣ ግን ከልብ ይወጣል፥ ሰውንም የሚያረክሰው ያ ነው። ከልብ ክፉ አሳብ፥ መግደል፥ ምንዝርነት፥ ዝሙት፥ መስረቅ፥ በውሸት መመስከር፥ ስድብ ይወጣልና። ሰውን የሚያረክሰው ይህ ነው» (ምቴ. ፲፭፥፲፯) ሲል በግልጽ አስተምሮናል። በዚህ መሠረት ክርስቲያኖች ከዚህኛው ጾም ላይ ሊበረቱ ይገባል። ይሁን እንጂ የትኛው ዐርበኛ ክርስቲያን ነው ከእነዚህ ከራሱ ከውስጡ ከሚወጡ የሚያረክሱ ነገሮች ጾሞ ርኩሰትን ድል የሚነሣ? ከዚህ በመቀጥል በፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፲፭ በአንቀጸ ጾም የተሰጠውን ሰፊውን የጾም ትምህርት ሕና ሥርዓት ሁሉ በዝርዝር እናገኛለን።
ከዚህ የሚከተለው ትምህርተ ጾም ለምእመናን ግልጽ እንዲሆንላቸውና ለአንባቢ አስልቺ እንዳይሆን በአርእስት ከመከፋፈሉና አንዳንድ ማብራሪያ የሚያስፈልግበት ቦታ ላይ አጫጫር ማብራሪያዎች በቅንፍ ከመጭመር በቀር በሙሉ ከፍትሐ ነገሥት የተወሰደና በ፲፭ኛው አንቀጽ የሚገኝ የቅዱሳን አበው ትምህርት ነው። በዚህ አንቀጸ ጾም በተሰኘው የፍትሐ ነገሥት ክፍል ውስጥ በርካታ ጥያቄዎች ለምሳሌ የአክፍሎት፣ የአሣ፣ የሩካቤ ሥጋ ወዘተ ጥያቄዎች ተመልሰው ይገኛሉ።
የጾም ትርጉም
ጾም ምንድን ነው? ለሚል ጾምስ፣ ጾም ግን፣ ጾምማ በደሉን ለማስተሥረይ፣ ዋጋውን ለማብዛት፤ እርሱን፣ ወዶ ሕግን ለሠራለት እየታዘዘ ፤ የፈቲውን ኀይል ያደክም ፡ ዘንድ [ሥጋም] ለነባቢት ነፍስ ትታዘዝ ዘንድ በሕግ ፡ ውስጥ ፡ በታወቀው ፣ ጊዜ፣ የሰው ፡ ከምግብ ፣ መከልከል ፡ ነው። ለክርስቲያን ሁሉ የታዘዘውም ጾም።
ሰባቱ አጽዋማት
፩ኛ/ ክብር ምስጋና ይግባውና ክርስቶስ የጾመው ጾመ ፵ (አርባ) ነው። ፋጻሚው ከፍሥሕ (የአይሁድ ፋሲካ) በፊት፡ ባለው፡ ዓርብ የሚሆን ነው። ከዚህም ቀጥሎ የስቅለት ሳምንት፡ ነው። እነዚህም፡ እስከ፡ አሥራ፤ ሁለት፡ ሰዓት፡ ድረስ፡ ይጾማሉ (ደም፡ የሚወጣው እንስሳ ከእንስሳትም) የሚገኘው አይበላባቸውም።
በአዋጅ ከሚጾሙት ሰባቱ አጽዋማት መካከል ይህ ጾም ዐብይ ጾም ፣ ጾመ ኢየሱስ ፣ ጾመ ሁዳዴ ፣ አርባ ጾም በመባል ይታወቃል።
ዐብይ ጾም መባሉ «ዐብይ» ማለት ታላቅ ማለት ነው ይኸውም ዐብይ ወይም ታላቅ አምላክ ክርስቶስ ስለ ጾመውነው። ለቤዛ ለካሣ የጾመልን እና ከመዳናችን ጋር የተያያዘ በመሆኑ አጽዋማቶቻችንን ሁሉ የባረከበት የቀደሰበት፣ ለጾማችን ኃይል ጉልበት የሰጠበት፣ በመጀመሪያ አብነት ለመሆን የጾመው ስለሆነና ከሌሎች አጽዋማት በቁጥርም ከፍ ስለሚል ዐቢይ ጾም ተብሏል። ጾመ ኢየሱስ መባሉም በቅዱስ መጽሐፍ እንደተጠቀሰ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመው በመሆኑ ጾመ ኢየሱስ ተብሏል (ማቴ ፬᎓፩)።
ሁዳዴ ጾምም ይባላል ይህ ስያሜ የወጣው «ሁዳድ» ከሚለው ሲሆን ሁዳድ ማለት በህብረት በብዙ ሕዝብ ተሳትፎ የሚሰበሰብ አዝመራ ያለበት ሰፊ የንጉሥ ወይም የሹም የእርሻ ቦታ ማለት ነው። ዐብይ ጾምም የሥላሴን ልጅነት ያገኙ ክርስቲያኖች በሙሉ የሚሳተፉበት ሰፊና ትልቅ በረከትን የሚቀበሉበት የአባታቸውን የንጉሥ ክርስቶስን መንግሥት የሚወርሱ ምእመናን ሁሉ የሚጾሙት ጾም በመሆኑ አባቶቻችን ጾመ ሁዳዴ ብለው ሰይመውታል።
፵ (አርባ) ጾም ተብሎም ይጠራል፣ ይኸውም ጌታ ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ ሔዶ ፵ ቀንና ፵ ሌሊት ጾመ፣ ጸለየ ተብሎ በቅዱስ መጽሐፍ እንደ ተጻፈ (ማቴ. ፬፤፪) ጌታ አርባ ቀን የጾመው ጾም ስለሆነ ነው።
ዐብይ ጾም ሦስት ክፍሎችና ስምንት ሳምንታት ያሉት ሲሆን እነሱም ፡- ሦስቱ ክፍሎች የተባሉት እነዚህ ናቸው፡፡
ዘወረደ (ጾመ ሕርቃል)፡- ይህም ጾሙ ከሚገባበት ሰኞ ጀምሮ እስከ እሁድ ድረስ ያለው ቀን ነው፡
የጌታ ጾም፡- ይህም ከቅድስት ሰኞ እስከ ሆሣዕና ዋዜማ ዐርብ ድረስ ያለው ፵ ቀን ነው።
ሕማማት፡- ይህም ጌታችን በአልዓዛር ቤት ለማዕድ ከተቀመጠበት የሆሣዕና ቅዳሜ ጀምሮ እስከ ቅዳሜ ሥዑር ያለው መከራን የተቀበለበት ፰ ቀን ሕማማት ነው፡፡ ይህም 7+40+8 = 55 ቀን ማለት ነው።
፪ኛ/ ዳግመኛም በእየ ሳምንቱ ሁሉ ዓርብና ረቡዕን መጾም ነው። በዓለ ፶ (ሃምሳ) የልደትና፣ የጥምቀት በዓል የተባበሩባቸው
(የዋሉባቸው) ጊዜ ፡ ካልሆነ ፡ በቀር ፡ እንደተጻፈው ፡ እስከ ፱ (ዘጠኝ) ሰዓት ፡ ድረስ ይጹሟቸው።
በዚህ ላይ የተጨመሩ፤ ሌሎች ጾሞች ፡ ግን በግብፅ ቤተ ከርስቲያን ፣ ተጽፈዋል። ከእነርሱም፡ እንደ፡ ዐቢይ ጾም ፤ በመጠንቀቅ የሚሆን (የሚጾም)፡ አለ፡ ይህችውም ከዐቢይ ጾም አስቀድማ የምትሆን፡ የሕርቃል (የዘወረደ ሳምንት) ጾም ናት።
፫ኛ/ ፫ (ሦስት) ቀን የነነዌ ሰዎች ጾም።
፬ኛ/ የልደትና የጥምቀት ዋዜማ ጾም (ገሐድ)።
፭ኛ/ ከእነርሱም የሚያንስ እንደ ረቡዕና ፡ እንደ ፡ ዓርብ የሚሆን ፡ አለ ፡ ይኸውም ፡ ከልደት አስቀድሞ ፡ የሚጾም ጾም ፡ ነው። መጀመሪያው የኅዳር እኩሌታ ፋሲካው የልደት በዓል ነው።
፮ኛ/ ከዚህም ቀጥሎ ፡ ከበዓለ ፶ ቀጥሎ ያለ የሐዋርያት ጾም ፡ ነው፤ ፋሲካውም : በጴጥሮስና በጳውሎስ ፡ በዓል ሐምሌ ፭ ቀን ነው። ያለሕጸጽም ሊጠብቋቸው (ሊጾሟቸው) ይገባል፡፡
፯ኛ/ ከእነዚህም ሌላ ብዙ ሰዎች ጠብቀው [አክብረው] የሚጾሙት አለ፡፡ ይኸውም ጾም ስለ እመቤታችን በዓል ነው። ይልቁንም መናኞች መነኮሳት የሚጾሙት መጀመሪያው ነሐሴ አንድ ቀን ፋሲካው የእመቤታችን በዓል ነው።
በእነዚህ በታዘዙት ጾሞች ከቀኑ እስከ ፱ (ዘጠኝ) ሰዓት ድረስ ይጹሙ። ከዓሣ በቀር ሥጋ አይብሉባቸው፡፡ (እዚህ ላይ ዓሣ ይበላል ማለት አይደለም፤ «ከአሣ በቀር» የሚለው በትርጉም ሊቃውንቱን ሲያከራክር የኖረ ስለሆነ ከፍትሐ ነገሥቱ ላይ ስላልታረመ ነው እንጂ ቅዱስ ሲኖዶስ እንዳይባላ ውሳኔ ሰጥቶበታል)፡፡ ከዚህ ከታዘዘው አብልጦ የጾመ ግን ዋጋው ይበዛለታል ከጥሉላት በቀር እሁድና ቅዳሜ አይጹሙ፡፡
ጾምስ የሥጋ ግብር ነው። ምጽዋት የገንዘብ ግብር እንደሆነ፡፡ ሕግ ጾምን ያስወደደው የፈቲው ጾር ትደክም ዘንድ ለነባቢት ነፍስም (ሥጋ) ትታዘዝ ዘንድ ነው፡፡
ጾም ይረባናል ብለን ከመጾማችን የተነሣ መንፈሳውያንን እንመስላለን፤ ከመሰልናቸውም የሚመስሉትን [ክርስቶስን] ለመምሰል ይቻላል። ዳግመኛም ጿሚው የረኃብን ችግር ያውቅ ዘንድ ነው። አውቆም ለተራቡትና ለሚለምኑት ይራራላቸው፡፡ ዳግመኛም በፅኑዕ ፈቃድ ሁኖ ሊመገበው ሥጋውንና ደሙን ይቀበል ዘንድ ነው። መቀበሉም በሥጋዊና በነፍሳዊ ትጋት ይሁን። ዳግመኛም ከእንስሳዊ ባሕርይ ተለይቶ የጾምን ሥርዓት ጠብቆ ከሰው ወገን ደግሞ በጸሎት የተለየ ሁኖ ስለ አጽዋም በተሠሩት ሕጎች የፀና ሁኖ በሁለንተናው እግዚአብሔርን ያምልከው፡፡
ጾመ ፵ (አርባ) በእናንተ ዘንድ የከበረ ይሁን፤ መጀመሪያውም ከሰንበቶቹ ሁለተኛ የሆነው ሰኞ ነው፡፡ መጨረሻውም ከፍሥሕ (የአይሁድ ፋሲካ) አስቀድሞ ባለው በዕለተ ዓርብ ነው፡፡ ይህም ከፍሥሕ ሱባዔ በኋላ ያለ ሱባዔ እንደሆነ ያስረዳል፡፡ ከዐቢይ ጾም በኋላ የከበረ ሰሙነ ሕማማትን ትፈጽሙ ዘንድ ትጉ፡፡
ከእርሷ በኋላ የፋሲካ ሳምንት የሚሆን ሰሙነ ፍሥሕ (የአይሁድ ፋሲካ) እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እንደዚሁም እነዚህን ስድስቱን ቀኖች እንጾም ዘንድ አዘዙን፡፡ በየሳምንቱም ረቡዕንና ዓርብን እንጾም ዘንድ አዘዙን። ይኸውም ምክር የተፈጸመበት ነውና። ይኸኛውም መድኃኒታችን ፈቃዱን ስለፈጸመበት ነውና፡፡ በሰባተኛው ቀን ዶሮ በጮኸ ጊዜ ከጾም ይረፉ።
ዘወትር በዕለተ ሰንበት መጾም አይገባም። እግዚአብሔር ከሥራው ሁሉ አርፎበታልና ቅዳሜ ስዑርን ብቻ ሊጾሙ ይገባል እንጂ፡፡ የፍጥረታቱ ሁሉ ፈጣሪ በመቃብር ውስጥ አድሮበታልና፡፡
በሊህ በስድስቱ ቀኖች ከቂጣ፣ ከጨውና ከውኃ ብቻ በቀር አይብሉባቸው፡፡ በሊህ ቀኖች ከወይን ከሥጋ ተለዩ፤ የኀዘን ቀኖች ናቸውና፤ የደስታ ቀኖች አይደሉም። ዓርብንና ቅዳሜን ግን ሁለቱንም በአንድነት ጹሟቸው። የሚችል እስከ ሌሊቱ ዶሮ ጩኸት ጊዜ ድረስ ምንም ምን አይቅመስባቸው፤ ሰው ሁለቱን ቀኖች በአንድነት ይጾም፤ ባይቻለው ግን የቅዳሜን ጾም ይጹም።
ጌታ ስለ ራሱ እንዲህ አለ “ሙሽራውን ከእነርሱ ለይተው በወሰዱት ጊዜ ያን ጊዜ ይጾማሉ” እናንተም በእነዚህ ቀኖች እስከ ሌሊት ድረስ ጹሙ፤ ሙሽራውን ከእኛ ለይተው በወሰዱት ጊዜ እኛ እንደ ጾምን፡፡
በዓለ ሃምሳን ከጨረሳችሁ በኋላ … ከዚህም ቀጥሎ ከአረፋችሁ በኋላ ጹሙ። ዳግመኛም ረቡዕንና ዓርብን ዘወትር ትጾሙ ዘንድ እናዝዛችኋለን። የሚቻላችሁስ ከሆነ ከእህል ከዚህ አብልጣችሁ ጹሙ፤ ለድሆችም ምጽዋት ስጡ፡፡
… ይህን መጽሐፍ ከሰበሰበው የተመረጠ ከሆነው መምህር ቃል የተገኘ ነው፡፡ የዚህ ሳምንት ምልክት ግን ልንበላበት እንደማይገባ እነሆ ረቡዕንና ዓርብን እንድንጾም ያዘዘበት አንቀጽ አለ። ዳግመኛም በዓለ ፶ (ሃምሳ)፣ ልደትና ጥምቀት ቢውልባቸው አትጹሙ ብሎ ያዘዘበት አንቀጽ አለ፡፡ ስለዚህ ሳምንት ግን አልተናገረም፡፡ ቢበሉባቸው በሚገባ ቀኖች ውስጥ ሊጾሙባቸው የማይገባ ቢሆን ኖሮ እንደነዚያ መልሶ በተናገረ ነበር።
ዳግመኛም እንዳንጾምባቸው እንዳንሰግድባቸው የታዘዝንባቸው ቀኖች እንደ እሑድ፣ እንደ ሰንበት [ቅዳሜ] እንደ ጌታ በዓላት ያሉ ቀኖች አሉና ከእነርሱ ጋር ይህን ሳምንት አልተናገረም። ዳግመኛም የሰሙነ ሕማማትን ሥራ ሳይሠራ ላለፈበት ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ስለርሷ መጾም መስገድ ይገባ ዘንድ ታዘዘ፡፡ ከበዓለ ሃምሳ በኋላ የሚውለው ሳምንት ይህ ቢሆን ኖሮ ከሃምሳ ቀኖች በኋላ ይበሉበት ዘንድ የሚገባ ቢሆን እንደገና ብሉበት በተባለ ነበር። በዓል አድርጉ ከማለቱ በቀር ብሉበት አላለምና። ይህስ በውስጡ ያሉትን የዓርብንና የረቡዕን ጾም ያስረዳል፡፡ እነርሱንም ይፈጽሟቸው ዘንድ አያስረዳም እነሆ ባስልዮስና አፈወርቅ እንዲህ አሉ። በዓል ማክበር በመብል አይደለምና ዳግመኛም በጾም በዓል ማክበር እንዲገባ የታወቀ ነው። ይኸውም ለበዓሉ የሚስማማው እንዲነበብ ነው እንጂ ሊበሉበት አይደለም። ኤጲስ ቆጶስ በተሾመ ጊዜ ፫ (ሦስት) ቀን እንድናከብር እነሆ ቀኖና አዘዘችን፡፡ በጾም ቀን እንኳ ቢሆን በእነዚህ በ፫ ቀኖች እንዳንበላ የታወቀ ነው፤ በዓል ማክበር በመብል አይደለም። ዳግመኛም ቢቻላችሁ ከዚህ አብዝታችሁ ጹሙ በማለታቸው ይህን ሕግ እነሆ ወሰኑ። በጾሙ ምክንያት ጠብ ክርክር ቢሆን መጾም ይገባል። ከመብላት በጣም ይሻላል።
ዳግመኛም ከተሰበሰቡት ወገን ቁጥራቸው ኸያ የሚሆኑት ጹመውታልና፤ ከእስክንድርያ ሊቃነ ጳጳሳት ወገን ከዚህ ቁጥር ቁጥራቸው እስከ በዙት ሊቃነ ጳጳሳት ድረስ በዚህ ሳምንት እነሆ ይህን ጾም ጾምን፡፡ የማኅበሩን ትእዛዝ ብንተላለፍ ይህን ማኅበር እንዲነቀፍ ብናደርግ ደግ አይደለም፡፡ ይልቁንም የሕጋችንን ትሩፋት በተቃወመ ጊዜ፡፡ ይኸውም ስለመብል ስስትን በመግለጽ የሚደረግ ክፋት ነው፡፡
ዳግመኛም ስለ ሃምሳኛው ቀን አከባበር ሙሴ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቀበለውን ሕገ ኦሪት ለሕዝቡ ከማስተማሩ በፊት እንደጾመ ጌታችንም በርሱ ላይ መንፈስ ቅዱስ ከወረደ በኋላ የርሱን ሕግ ለሕዝብ ከማስተማሩ አስቀድሞ እንደዚሁ ጾመ፡፡ ሐዋርያትም በበዓለ ፶ (ሃምሳ) መንፈስ ቅዱስ በወረደላቸው ጊዜ ሕገ ወንጌልን ለሕዝብ ከማስተማራቸው አስቀድሞ እንደዚሁ ጾሙ፡፡ እኛም በዚህ በእነርሱ ተመራን፡፡
ልደት በጾም ቀኖች ማለትም ረቡዕና ዓርብ ቢውል ይጸልዩ። ሥጋውንና ደሙንም ይቀበሉ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ ጹሙ ብለው አይፍረዱ።
አንድ ሰው በባሕር ቢኖር ሰሙነ ሕማማትን ባያውቅ ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ይጹም። ይኸውም ሰሙነ ሕማማትን የሚጠብቅ አይደለም፡፡ ምሳሌውን ብቻ ነው እንጂ ስለእርሱ መጾም ይገባዋል፡፡
ዐቢይ ጾምንና ዓርብን ረቡዕን የማይጾም የታወቀ ደዌ ያለበት ካልሆነ በቀር ካህን ከሆነ ይሻር ሕዝባዊ ቢሆንም ይለይ፡፡
ካህን ሰሙነ ሕማማትን ቀንና ሌሊቱን ሳያስተካክል [ያለቀኑ] አስቀድሞ ቢያውል ይሻር፡፡ ከሕማማት ቀጥላ ከምትሆን ከቅዳሜ ስዑር በቀር እሑድንና ቅዳሜን የጾመ ካህን ቢኖር [ከሹመቱ] ይሻር፡፡
በአርባ ጾም ሠርግ ማድረግ አይገባም። ሴትም በወለደች ጊዜ ሰውን ወደ መጠጥ ቤት መጥራት አይገባም፡፡
ከካህናት ወገን ማንም ቢሆን በአርባ ጾም በዓርብና በረቡዕም ጾም ወይን መጠጣት አይገባውም ወደ መዋት (ውሽባ ቤት) አይግባ፡፡ በዐቢይ ጾም ወራት ሰው ከሚስቱ ጋር አይተኛ።
በጾም ጊዜ የሰማዕታት በዓል አከባበር ቀኖና
በዐቢይ ጾም የሰማዕታትን በዓል ልናከብር አይገባንም፡፡ የሰማዕታት መታሰቢያ በእሑድ በቅዳሜ ይሁን እንጂ፡፡ የሰማዕታት በዓል ከጾም ላይ ቢውል ስለ ሰማዕታት ሞት ምክንያት ኤጲስ ቆጶሱ ወይም ቄሱ ለሕዝቡ በመብል በዓል ቢያከብር ይሻር፡፡ እርሱ ለብዙዎች ሰዎች የኃጢአት ምክንያት ሆኗልና። እነርሱ በፈቃዳቸው ቢበሉ ግን ኤጲስ ቆጶሱ ወይም ቄሱ ይለያቸው፡፡ በጾም ወራት ከሆነ በሰማዕታት በዓል ቀን በመብል በመጠጥ ማክበር አይገባቸውምና። እነዚህ ሰማዕታት እየተራቡ እየተጠሙ በእሳት ተቃጥለው ሞተዋልና።
የልደት የጥምቀትና የበዓለ ሃምሳ ቅዳሴ ቀኖና
ስለ ልደትና ስለ ጥምቀት ግን በዚያ ዘመን በኒቅያ የተሰበሰቡ ሊቃውንት ቅዳሴው በሌሊት ይሆን ዘንድ አዘዙ፡፡ ዳግመኛም በበዓለ ሃምሳ እንደዚሁ ነው።
የዐቢይ ጾም ሠዓቶች
ክብርት በምትሆን በአርባ ጾም በመጀመሪያው ሱባዔ ፀሐይ እስኪገባ ድረስ ይጹሙ፡፡ የመጀመሪያው ሱባዔ ካለፈ በኋላ እስከ ፲፩ (አሥራ አንድ) ሰዓት ድረስ ይጹሙ፡፡ በሰሙነ ሕማማት ግን ኮከብ እስኪወጣ ድረስ ይጹሙ፡፡
በዐቢይ ጾም የጌጥና የሩካቤ ቀኖና
በእነዚህም ወራቶች አያጊጡ። ሴቶችም ጌጣቸውን ይተው፡፡ ሁሉም ለእያንዳንዱ በአርባ ጾምና በሰሙነ ሕማማት መጠበቅ ይገባዋል፤ ድኅነታችንና የኃጢአታችን ሥርየት በእነርሱ [በዐብይ ጾምና በሰሙነ ሕማማት] ነውና፡፡ ይኸውም ሥራ አንዱስ እንኳ በአርባ ጾም ወራት በምንጣፍ ፈጽሞ እንዳይገናኝ [ቢገናኝ ግን] ከጋብቻ ሕግ የወጣ ነው፡፡ ክብርት በምትሆን በሕማማት ወራት ይህችን ኃጢአት የሚሠራት ሰው ወዮለት። በአርባ ጾም በተድላ በደስታ ፈቃዳችንን ካደረግን ትንሣኤውን ባየን ጊዜ ተድላ ደስታችን ወዴት አለ?
የተሻለው ጾም!
ጾም ከእህል ከውኃ መከልከል አይደለም። ከእግዚአብሔር ፊት የሚደርስ ጾምስ የልብ ንጽሕና ነው። (ኢሳ. ፶፷፤ ማቴ. ፲፭፥
፲፮)። ሥጋ ቢራብ ቢጠማ ነፍስ ግን ፈቃዷን ብትፈጽም ልብም ከጣዕሙ የተነሣ ደስ ቢለው የጾምህ ጥቅሙ ምንድን ነው? በተባሕትዎ በትሕትና አርባ ቀን ጾምን ይጹሙ፡፡ ከጥሉላት መከልከል ይገባል፡፡ አያግቡም፡፡
የሰሙነ ሕማማት ቀኖና
በሰሙነ ሕማማት ክርስትና ማንሣት፣ ክህነት መስጠት፣ [በዚሁ ሰሙነ ሕማማት ውስጥ] ለሞቱ ሰዎች መጸለይ አይገባም። በእነዚህም ቀኖች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ፈጽሞ ማገልገል ይገባል እንጂ። በሰሙነ ሕማማት ስለሚሞቱት ሰዎች የሙታን ግንዘት፣ የሐዋርያት ሥራ፣ ወንጌላትና የሙታን ፍትሐት በሆሣዕና በዓል ቀን ይነበብ እንጂ።
በጸሎተ ሐሙስ ጸሎተ ተአምኆ እግዚአ ሕያዋን የቡራኬ ጸሎት አይባልም (አይጸለይም)። ቅዳሜ ግን እግዚአ ሕያዋን ይባላል ፍትሐት ይፈታል። ከመሳለም በቀር ጸሎተ ዕጣንም ይጸለያል። በዕለተ እሑድ ግንዘት ማድረግ በፋሲካ ቀንም ማልቀስ አይገባም፡፡ ዳግመኛም በውስጧ በአርባ ጾም ከተድላ ከደስታ ወገን ምንም ማድረግ አይገባም፡፡ መጋባት፣ ክህነት መስጠት፣ ክርስትና ማንሣትና ከሹመትም ወገን፤ ስለሚሞቱት ከመጸለይ በቀር ምንም ማድረግ አይገባም። ይሞታል ተብሎ ለሚያስፈራው ግን ጥምቀተ ክርስትና ይደረግለታል።
ዐቢይ ጾም ስምንት ሱባዔ እንደሆነ በነገሥታት መጽሐፍ ተጻፈ፡፡ መጀመሪያው የክረምት መጨረሻ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ክረምት እንዳይደለ ይታወቃል። መጨረሻው የበጋ መጀመሪያ ነው። በየሳምንቱ አምስት ቀን መጾም ይገባል።
የዐርባና ረቡዕ ቀኖና
በብሉይ ሕግ በዓል በቅዳሜ በሐዲስ ሕግ በዓል በእሑድ ይብሉ። ቅመማት የበዛበትን አይብሉ፡፡ የዓርብንና የረቡዕን ጾም ግን ከልደት ከጥምቀት ከበዓለ ሃምሳ በቀር ዘወትር ይጹሙ፡፡ ከእሑድና ከቅዳሜ በቀር ለእግዚአብሔር የሚታዘዙ ሰዎች ከበዓለ ሃምሳ በኋላ የሐዋርያት ጾም መጾም ይገባቸዋል።
ማጠቃለያ
እንግዲህ የምንጾበት ዋና ዓላማ “ ጾም ወጥንተ ኩሉ ገድል ሠናይት ” እንዳለ (ማር ይስሐቅ) ጾም የበጎ ሥራ ሁሉ መሠረት፣ የመንፈሳዊ ኅይልና የጽድቅ ምንጭ ስለሆነ ነው።
ጌታችን ከማስተማር ሥራው አስቀድሞ ከጥምቀቱ አስከትሎ የመጀመርያ ተግባሩ ጾም ነበር። ያመነ የተጠመቀ ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያንም በጥምቀት ያገኘውን ልጅነት በምግባር በትሩፋት ለመግልጽ ተቀዳሚ ተግባሩ ጾም ነው።
የጾም መሠረታዊ ዓላማ መራብ ሳይሆን ከምግብ በመከልከል ፍቃደ ሥጋን አድክሞ ለፈቃደ ነፍስ ማስገዛት፣ ሰውነት ለበጎ ሥራ እንዲታዘዝ እንዲገራ ማድረግ ነው። ለዚህም ነው ማር ይስሐቅ ጾምን «ወጥንተ ኩሉ ገድል ሠናይት» የሚላት። የተወደዳችሁ ክርስቶሳውያን ጾምን የምንጾመው በጎ ሥራን ለማብዛትና ጌታችን በወንጌል «ጽድቅን [ስለ ጽድቅ] የሚራቡና
የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፥ ይጠግባሉና» (ማቴ. ፭፥፮)። እንዳለው ለምጽደቅ ነውና ጾማችን እንደ ዘመኑ የረሀብ አድማ ብቻ ሆኖ እንዳይቀር የሚያጸድቅና እና የእግዚአብሔርን የጦር ዕቃ ሁሉ የሚያስታጥቅን እንድናደርገው እንትጋ።
ጾማችን ለሀገራችን ለኢትዮጵያ ሰላምን፣ ለቤተ ክርስቲያናችን አንድነትን፣ ለእየራሳችን ለየቁጥራችን ሥርዬተ ኃጢአትን፣ ረድኤት በረከትን የሚያስገኝ እንዲሆንልን እግዚአብሔር አምላካችን ይርዳን።
አባ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ
፳፻፲፭ ዓ/ም