ገብርኄር (የዐቢይ ጾም ስድስተኛ ሳምንት)

ታላቁን የጌታችንን ጾም ከጀመርን ስድስተኛ ሳምንት ላይ ደርሰናል፡፡ ይህን ሳምንት ቅድስት ቤተክርስቲያን ”ገብርኄር” የሚል ስያሜ ሰጥታዋለች፡፡ ገብርኄር በጎ አገልጋይ ማለት ሲሆን የስያሜውን መነሻ የምናገኘው በዕለቱ ሥርዓተ ቅዳሴ ከሚነበበው የወንጌል ክፍል ማቴ. 25:14-30 ነው፡፡

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምሳሌ መስሎ ካስተማራቸው ትምህርቶች መካከል አንዱ የሆነው ይህ የዛሬው ወንጌል አስተማሪ የሆኑ መሠረታዊ ጉዳዮችን በውስጡ ይዟል፡፡ በተለይ ምንም እንኳን የቤተክርስቲያን ሓላፊነት የእገሌና የእገሊት ተበሎ ባይወሰንም ቤተ ክርስቲያን ባላት የአገልግሎት መዋቅር መሠረት የሓላፊነትን ቦታ ይዘው ለሚያገለግሉ ሰዎች አትኩሮት ሊሰጡባቸው የሚገባቸውን ነጥቦች ይጠቁማል፡፡ ይህን ለማየት ያመቸን ዘንድ ከታሪኩ የመጀመያ ክፍል በመነሣት ዋና ዋና የሆኑ ዐሳቦችን በአትኩሮት መመርመር  ጠቃሚ ነው፡፡

በምሳሌያዊው ታሪክ መጀመሪያ ላይ የምናገኘው አንድ መንገድ ሊጀምር ያሰበ ሰው ከመሔዱ በፊት አገልጋዮቹን ጠርቶ ለእያንዳንዳቸው እንደ ችሎታቸው መጠን ለአንዱ አምስት ለአንዱ ሁለት እንዲሁም ለሌላኛው አንድ መክሊት ነግደው ያተርፉበት ዘንድ እንደሰጣቸው ነው፡፡ ገና ከታሪኩ መጀመሪያ እንደምንረዳው የአገልጋዮቹ ጌታ ምንም እንኳን እርሱ ለመንገድ ቢዘጋጅም ሀብቱ ግን በተዘጋ ቤት ውስጥ ተቆልፎበት እንዲቀመጥ አልፈለገም፡፡ በዚህም አገልጋዮቹን ጠርቶ ገንዘቡን በአደራ ተቀብለው እንዲያተርፉበት ማዘዙን እንደማስረጃ ልናቀርብ እንችላለን፡፡ ሆኖም ግን ማትረፍ በመፈለጉ ብቻ ገንዘቡን ያለአግባብ አልበተነም፡፡ ነገር ግን ለእርሱ ቀረቤታ የነበራቸውን አገልጋዮቹን ጠርቶ ያውም እንደየችሎታቸው መጠን ሓላፊነቱ ሳይከብዳቸው እንዲሠሩበት ገንዘቡን አከፋፈላቸው፡፡

ይህ ጌታ ቅንነትና ርኅራኄ የበዛለት እንደሆነ የሚያመላክተን ነገር አለ፡፡ ይኸውም ለአገልጋዮቹ ሓላፊነትን ቢሰጥም እንኳን ከእነርሱ ጋር በነበረው ቀረቤታ ማን ምን መሥራት ይችላል የሚለውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ለእያንዳንዳቸው እንደ ሓላፊነት የመሸከም አቅማቸው አምስት ሁለት አንድ እያደረገ መስጠቱ ነው፡፡ ምናልባት ስስት ባልተላቀቀው ስሜት ለሚያስብ ሰው የዚህ ጌታ መክሊት አሰጣጥ አድልዎ ያለበት ሊመስለው ይችላል፡፡ ታሪኩን እስከ መጨረሻው ብንከታተለው ግን የሚያሳየን የባለ መክሊቱን ባለቤት ቅንነት ነው፡፡ ቀጥለን እንደምናነበው ይህ ጌታ ለአገልጋዮቹ አትርፉበት ብሎ መክሊቱን ሰጥቷቸው በሔደበት ሀገር አልቀረም፡፡ ይልቁንም እያንዳንዱ በተሰጣቸው መክሊት ምን እንደሠሩበት ሊቆጣጠራቸው እንደመጣ እናነባለን፡፡ ስለዚህ አገልጋዮቹ በሰጣቸው መክሊት ምን እንደሠሩ እንደሚጠይቃቸው እያወቀ ከአቅማቸው በላይ የሆነ መክሊትን በመስጠት ምን ሠርተው የተሰጣቸውን መክሊት ያህል ማትረፍ እንደሚችሉ በማሰብ እንዲጨነቁ አልፈለገም፡፡ በተቃራኒው የምናየው ያለምንም ጭንቀት ከአእምሯቸው በላይ ሳይሆን ባላቸው ኀይል ተጠቅመው መሥራትና ማትረፍ የሚችሉትን ያህል መክሊት እንደሰጣቸው ነው፡፡

ከብዙ ጊዜም በኋላ የእነዚያ አገልጋዮች ጌታ በሰጣቸው መክሊት ምን እንደሠሩበት ሊቆጣጠራቸው ሲመጣ አምስት መክሊት ተቀብሎ የነበረው ሌላ አምስት እንዲሁም ሁለት መክሊት ተቀብሎ የነበረው ሌላ ሁለት መክሊት አትርፎ ጌታቸው ፊት እንደቆሙ ያ ጌታም በእነዚህ አገልጋዮቹ ታማኝነት ተደስቶ ወደ ደስታው እንዳስገባቸው እናያለን፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ያ አንድ መክሊት ተቀብሎ የነበረው ምድርን ቆፍሮ ያተርፍባት ዘንድ የተሰጠችውን መክሊት እንደቀበረ ከዚህም አልፎ ምን አደረክባት ተብሎ ሲጠየቅ የአመጽ ንግግር እንደተናገረ በዚህ ከፊቱ ያዘነው ጌታውም ያን ክፉ አገልጋይ እንዲቀጣ እንዳደረገው አናነባለን፡፡

በዚህኛው ክፍል ከተጠቀሰው ታሪክ ሦስቱን አካላት ማለት የመክሊቱን ሰጪ ጌታ፣ በጎ የተባሉ አገልጋዮችና ክፉ እና ሰነፍ የተባለውን አገልጋይ በተናጥል እንመልከታቸው፡፡

1. የአገልጋዮቹ ጌታ፡

ይህ ሰው ለገንዘቡ ጠንቃቃ ከመሆኑ ባሻገር በአገልጋዮቹ ላይ ሙሉ ሥልጣን እንዳለው እናያለን፡፡ በክፉው አገልጋይ ላይ ባለመታዘዙ ምክንያት የፈረደበትን ፍርድ /ልቅሶና ጥርስ ማፏጨት ወዳለበት በውጪ ወዳለ ጨለማ እንደአወጡት/ ስንመለከት የሚያሳየን የአገልጋዮቹን ጌታ ታላቅ ሥልጣን ነው፡፡ ምንም እንኳን ሥልጣኑ ጽኑ ቢሆንም ይህ ጌታ ፍርዱ ግን በእውነት ላይ የተመረኮዘ መሆኑን ደግሞ በድካማቸው ታግዘው በተሰጣቸው መክሊት ላተረፉት በጎ አገልጋዮች የሰጣቸውን ፍጹም ደስታ መጥቀስ ይቻላል፡፡

2. በጎ አገልጋዮች:-

በአገልጋዮቹ ጌታ በጎ አገልጋዮች የተባሉት አምስት መክሊት የተቀበለውና ሁለት መክሊት የተቀበለው ናቸው፡፡ እዚህ ጋር ማስተዋል የሚገባው እነዚህ ሁለቱ አገልጋዮች በጎ አገልጋዮች ለመባል ያበቃቸው አስቀድመው ብዙ ወይንም የተሻለ ቁጥር ያለው መክሊት ለመቀበል መብቃታቸው አይደለም፡፡ ጉዳዩ የመክሊቱ ቁጥር ሳይሆን በተሰጣቸው መክሊት መጠን የሚገባቸውን ያህል ደክመው ማትረፍ መቻላቸው ነው፡፡ ወይንም ያ ባለ አንድ መክሊት አገልጋይ ከሁለቱ ያሳነሰው ከአንድ በላይ መክሊት መቀበል የማይችል መሆኑ ሳይሆን በዚያችው በአንዷ መክሊት እንኳን መሥራት አለመቻሉ ነው፡፡

3. ክፉና ሰነፍ አገልጋይ:-

ይህ ሰው የተጠቀሱ ሦስት መሠረታዊ ችግሮች አሉበት፡፡

  1. የአገልጋዮቹ ጌታ ወደ መንገድ ሊሔድ በተዘጋጀበት ወቅት አገልጋዮቹን ጠርቶ ለእያንዳንዳቸው እንደችሎታቸው ገንዘቡን ሲሰጣቸው አትርፈው እንዲቆዩት ነው፡፡ ከላይ እንደተነገጋገርነው እንደ አቅማቸው መስጠቱም አቅማቸው በሚፈቅደው የሥራ ደረጃ እንዲሰማሩ በማሰብ ነበር፡፡ ይህ ሰነፍ አገልጋይ ግን ያደረገው ከታዘዘበት ዓላማ በተቃራኒው መልኩ ነው፡፡ ሊሠራበት የሚገባውን መክሊት ቀበረው፡፡ ይህም ለጌታው ትዕዛዝ ያለውን ቸልተኝነት ያሳያል፡፡
  2. ጌታው በመጣ ጊዜ አመጽ የተመላበት የሐሰት ንግግር ተናግሯል፡- ከሔደበት ቦታ ተመልሶ ጌታው በተሰጠው መክሊት ምን እንዳደረገ ሲጠይቀው «አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ፣ ካልበተንህበትም የምትሰበሰብ ጨካኝ ሰው እንደ ሆንህ አውቃለሁ ስለፈራሁም ሔድሁና መክሊትህን በምድር ውስጥ ቀበርሁ፡፡» ሲል መለሰለት፡፡ ይህ ንግግር ከአመጽ ንግግርነቱ በተጨማሪ ውሸት አለበት፡፡ ምክንያቱም እርሱ እንዳለው ጌታው ካልዘራበት የሚያጭድ ካልበተነበት የሚሰበሰብ ጨካኝ ሰው ቢሆን ኖሮ ያደርግ የነበረው ምንም መክሊት ሳይሰጠው ከነትርፉ ሁለት መክሊቶችን ይጠይቀው ነበር፡፡ ነገር ግን ተጽፎ የምናነበው ትርፉን ከመጠየቅ በፊት አንድ መክሊት ሰጥቶት እንደበረ ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ አስቀድሞ ገንዘቡን ዘርቶ ነበር ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ጌታ ዘርቷልና ማጨድ ይገባዋል፤ በትኗልና መሰብሰብም መብቱ ነው፡፡
  3. እርሱ መሥራት ሲሳነው እንኳን ዕድሉን ለሌሎች አልሰጠም፡- ይህ ሰው የተሰጠው መክሊት በትርፍ ሊመለስ እንደሚገባው ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ምክንያቱም ገና ሲቀበል ከጌታው የተቀበለው ትዕዛዝ ነውና፡፡ ስለዚህ ምንም እንኳን መውጣት መውረዱ ቢከብደውም ወጥተው ወርደው ማትረፍ ለሚችሉ ሰዎች አለመስጠቱ ተጨማሪ ጥፋቱ ነው፡፡ ይህን እንዳያደርግ ያሰረው ደግሞ ውስጡ የተቀረጸው የአመጽ መንፈስ ነው፡፡ ጌታው መጥቶ ስለ ትርፉ ሲጠይቀው የሚመልስለትን ረብ የለሽ ምክንያት እንደ መከላከያ አድርጎ ማሰቡ አእምሮው ሌላ አማራጭ እንዳያስብ የዘጋበት ይመስላል፡፡

የመጽሐፍ ቅዱስ መተርጉማን አባቶች የዚህን ምሳሌያዊ ታሪክ ምስጢር ሲያስተምሩ የአገልጋዮቹ ጌታ የፍጡራን ጌታ የሆነ የእግዚአብሔር ምሳሌ እንደሆነ እንዲሁም ሦስቱ አገልጋዮች በተለያየ ደረጃ ያሉ ምዕመናንን እንደሚወክሉ ያስተምራሉ፡፡

ከዚህ የወንጌል ክፍል ምን እንማራለን?

ከተጠቀሰው ታሪክ የምንማራቸው ብዙ ነገሮች ቢኖሩም ዓበይት የሆኑትን ሁለቱን እንመልከታቸው፡፡

  1. ለእያንዳንዳችን ከእግዚአብሔር የተሰጠ ስጦታ እንዳለ እንረዳበታለን

እግዚአብሔር እያንዳንዳችን በሃይማኖት ሆነን የምናፈራውን ፍሬ ይፈልጋል፡፡ ምንም እንኳን ከእኛ ፍሬን ቢፈልግም ያን ፍሬ ማፍራት የምንችልበትን ኃይል ግን የእግዚአብሔርን ልጅነት ካገኘንበት ከዕለተ ጥምቀት ጀምሮ እንደሚያስፈልገን መጠን እየሰጠን ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቀበልናቸው ስጦታዎች በቁጥር እጅግ ብዙ ቢሆኑም በዓይነታቸው ግን ለሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው እያንዳንዱ ክርስቲያን ዳግመኛ በመወለድ ምስጢር ያገኘው የእግዚአብሔር ልጅነት ጸጋና ከልጅነት ጋር በተያያዘ የሚሰጡ ስጦታዎች ናቸው (ዮሐ.3፥3)። ሁለተኛው ዓይነት ደግሞ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድና እንደ ሰውየው አቅም ለተለያዩ መንፈሳዊ አገልግሎቶች ማስፈፀሚያ ይሆኑ ዘንድ በእግዚአብሔር የሚሰጡ ስጦታዎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ ትንቢት መናገር ፣ በተለያዩ ልሳናት መናገር ፣ አጋንንትን ማስወጣት … የመሳሰሉት ከዚህኛው ዓይነት ስጦታ የሚመደቡ ናቸው (1ኛ ቆሮ.12፥4)፡፡

በመጀመሪያውም ይሁን በሁለተኛው ዓይነት ስጦታ ተቀባዮች ዘንድ ግን ብዙ የሚያሳዝኑ ችግሮች አሉ፡፡ በዳግመኛ መወለድ ምሥጢር (በ40 ና 80 ቀን ጥምቀት) ስላገኘነው የልጅነት ጸጋ ጊዜ ሰጥቶ የሚያስብ ክርስቲያን ማግኘት በዚህ ዘመን በጣም አዳጋች ነው፡፡ በዓመት ውስጥ ክርስቲያንነቱ ለጥምቀት በዓልና ለመስቀል ደመራ ካልሆነ ትዝ የማይለው ቁጥሩ ቀላል አይደለም፡፡ ከዚህ የከፋው ደግሞ ከቤተ ዘመድ አንድ ሰው ምናልባትም ራሱም ሊሆን ይችላል ነፍሱ ከሥጋው ካልተለየች ወደ ቤተ ክርስቲያን ደጅ ብቅ አይልም፡፡

እግዚአብሔር ለእኛ የልጅነትን ጸጋ በመስጠቱ ለእኛ ያለውን ጥልቅ ፍቅሩን አሳይቶናል፡፡ ምክንያቱም ልጅነታችን ዋጋ ተከፍሎበታልና፡፡ እንዲሁ በቀላሉ አይደለም ልጆች የተባልነው፡፡ እኛ ልጅነትን እንድንቀበል አምላክ መከራን ተቀብሏል፡፡ የጥምቀታችን ውሃ የፈሰሰው በጦር ከተወጋው ከጌታ ጎን ነው (ዮሐ.19፥24)፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ይሄንን ሁሉ ሲያመለክት ”የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ልንጠራ አብ እንዴት ያለውን ፍቅር እንደሰጠን እዩ፡፡” (1ኛ ዮሐ.3-1) እኛ ልጆቹ እንሆን ዘንድ እግዚአብሔር ካሳየን የአባትነት ፍቅር በተጨማሪ ልጆቹ ስለመሆናችን የገባልንም ተስፋ ከአዕምሮ በላይ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለገላትያ ምዕመናን በላከው መልእክቱ ”እንኪያስ እናንተ ልጆች ናችሁ እንጂ ባሮች አይደላችሁም፡፡ ልጆች ከሆናችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ወራሾች ናችሁ፡፡” (ገላ.4:7) በማለት  ስለሚጠብቀን ተስፋ ነግሮናል፡፡

ስለዚህ በጣም ልንጠነቀቅበት የሚገባን የመጀመሪያው መክሊታችን ልጅነታችን መሆኑን መረዳት ያስፈልገናል፡፡ በዚህም መክሊት እንድንሰራ የታዘዝናቸውን ምግባራት እንድናፈራ የሚጠበቅብንን ፍሬዎች ማፍራት አለብን፡፡ ያለበለዚያ መክሊቱን እንደቀበረው ሰው መሆናችን ነው፡፡

  • እያንዳንዱ ስጦታ እንደሚያስጠይቅ እንረዳለን

እግዚአብሔር ያለ አንድ አላማ ለሰዎች ሓላፊነትን የሚያሰከትል ስጦታ አልሰጠም አይሰጥምም፡፡ ማንም ከእግዚአብሔር የተቀበለ ሰው የተሰጠው ስጦታ ለሆነ አላማ ነውና ጥያቄ አለበት፡፡ ጠያቂው ደግሞ የስጦታው ባለቤት ራሱ እግዚአብሔር ነው፡፡ ስለዚህ ማንም ይሁን ማን ግን ስለተሰጠው መክሊት ባለቤቱ ከፊቱ አቁሞ እንደሚጠይቀው መዘንጋት የለበትም፡፡እንግዲህ በአጠቃላይ መክሊት የተባለ ጸጋ ስጦታ ሲሆን እግዚአብሔር ለእያንዳንዳችን የተለያየ ስጦታ ሰጥቶናል፡፡ በተሰጠንም ስጦታ ልናገለግልበት ያስፈልጋል፡፡ በተጨማሪ መክሊት ቃለ እግዚአብሔር ነው፡፡ የሰማናትን ቃለ እግዚአብሔር ለሌላው ማሰማት ይገባናል ፡፡ ከእኛ የሚጠበቀው ማሰማቱ ብቻ ነው፡፡ በልቦናው አድሮ ሥራ የሚሠራ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ነውና፡፡ በመሆኑም እርሱ በሰጠን የአገልግሎት በር ጸጋ በታማኝነት በማገልገል በሕይወት ዘመናችን ሁሉ መንፈሳዊውን ሀብት የምናተርፍ እንሆን ዘንድ የተላለፈልን አምላካዊ ምክር ነው፡፡ ምክንያቱም እኛ የተጠራነው ፍሬ ልናፈራና ሌላውንም ልናተርፍ መልካም ሥራን ልንሠራ እንጂ የሥጋችንን ፈቃድ በመከተል የኃጢአት ባሮች ልንሆን አይደለም፡፡ መጽሐፍ እንደሚነግረን  ¨ሁሉ እንደተጠራ እንዲሁ ይኑር” (፩ኛ ቆሮ. ፯፥፳) ይላልና።

አሁን ባለንበት ወቅት በጎና ታማኝ አገልጋይ መሆን እንዳንችል ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ የችግሮቹም መሠረታዊ ምንጭ በተጠሩበት ጸንቶ መቆም ፈጽሞ አለመቻልና ለሥጋዊ ጥቅም ብቻ በማድላት ሓላፊነትን መዘንጋት ናቸው፡፡ በሥጋዊ አምሮት ፍላጎትና ምርጫ ውስጥ ደግሞ መንፈሳዊ ጸጋንና በረከትን ለማግኘት የሚያስችለንን የታማኝነት ሥራን መሥራት አይቻልምና በታማኝነት ከምናድነው ሰው ይልቅ መክሊታችንን በመቅበር ባለመታመን መሰናክል የምንሆንበት ሰው ሊበዛ እንደሚችል አያጠራጥርም፡፡ በመሆኑም ከእርሱ ዘንድ እንደ ዓቅማችን የተሰጠንን መንፈሳዊ ዕውቀት ሀብትና አገልግሎት ለሌላው በማድረስ መክሊታችንን ልናበዛ የምንችለውና አገልግሎታችን ወይም ክርስትናችን ውጤታማ የሚሆነው ምርጫችንን አውቀን እንደቃሉ ሆነንና ጸንተን ስንገኝ ብቻ ነው፡፡ ይህ ባለመሆኑ ነው ዛሬ ብዙዎቻችን በሕይወታችን ሌላውን ማትረፍ አቅቶን በእግዚአብሔርና በሰውም ዘንድ በሚያስወቅስ የስንፍና መንገድ ላይ ቆመን የምንገኘው፡፡ ስለዚህም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው “ጌታችሁ በምን ሰዓት እንዲመጣ አታውቁምና እንግዲህ ንቁ” (ማቴ. ፳፬፥፵፪) ብሎናል፡፡

ቃሉን የሰማንና የምናውቅ ሁላችን በሞቱ ላዳነን፣ በልጅነት ጸጋም ላከበረን፣ በትንሣኤውም ላረጋጋን፣ በመስቀሉ ጥልን ገድሎ ከራሱ ጋር ላስታረቀን፣ በውኂዘ ደሙም ሕይወትን፣ ሰላምን፣ ፍቅርን፣ በረከትንና ዘለዓለማዊ ደስታን ለሰጠን አምላካችን በመታዘዝ አቅማችን በሚፈቅደው አገልግሎት ጸንቶ መገኘት ተገቢ ነው፡፡ በአገልግሎት የመጽናት ምልክቱ ደግሞ አትራፊነት ነው፡፡ ቅዱሳን ነቢያት፣ ቅዱሳን ሐዋርያት፣ ቅዱሳን ሊቃውንት በቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ በአትራፊነት ይታወቃሉ፡፡ ለማትረፍ ግን ራሳቸውን ለእውነት ለአገልግሎት ለመከራ አሳልፈው በመስጠት ነው፤ በትንሹ መታመን ሲባል የእኛ አገልግሎት ከፈጣሪ ቸርነት ጋር ስለማይመጣጠን ነው፤ በብዙ እሾምሃለሁ ማለቱም በመንግሥተ ሰማያት ለዘለዓለም ከብሮ መኖርን ነው፡፡

ከቅዱሳን ነቢያትም ሐዋርያትም ሰብአ አርድእትም ሊቃውንትም የሰማነውና ያየነው እውነት ምንጊዜም ትጉህ ሠራተኛ የሚሠራው መልካም ሥራ ሁሉ ለቤተ ክርስቲያንም ለሀገርም የሚሰጠው ጥቅም እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ ዘመን ልዑል እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን፤ ምእመናንን፤ ሀገርንና ሕዝብን ለመምራት የጠራንና የመረጠን፤ በአገልግሎት ዐደባባይ ያስቀመጠን ሰዎች እጅግ ዕድለኞች ነን፤ ምክንያቱም የሕዝብን ችግርና አቤቱታ ሰምቶ ተቀብሎ መፍትሔ መስጠት ትርፋማነት ነውና፤ ትርፋማነት ደግሞ ወደ ትልቁ የሹመት መሰላል መውጣት ነው፤ ይህ ሳይሆን ቀርቶ አገልግሎታችን ተደናቅፎ የሕዝባችን ችግር ሳይፈታ ቀርቶ የአገልግሎታችን ተቆጣጣሪ አምላካችን ቢጎበኘን “አንተ ሰነፍ አገልጋይ” ተብለን ወደ ውርደት አዘቅት እንዳንላክ መጠንቀቁ አይከፋም፡፡ የመሾም የመሻር የማሳደግና የማውረድ ሥልጣን የእግዚአብሔር ነውና፡፡ “ከእናንተ መካከል አንዱን እንኳ እንዳናስቸግር ቀንም ሌሊትም እንሠራ ነበር” (፩ኛ ተሰ. ፪፥፱) በጎና ታማኝ አገልጋዮች ሆነን እንድንገኝ ጠንክረን ልንሠራ ይገባናል፡፡

                                         ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!